“Systematic Review and Meta Analysis” በሚል ርዕስ የፅህፍ ስራዎችን ሳይንሳዊ አጠቃሎ ለማቅረብ የሚያስችል የተግባር ስልጠና እየተሰጠ ነው ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የተለያዩ የፅሁፍ ስራዎችን ሳይንሳዊ አጠቃሎ ለማቅረብ የሚያስችል የተግባር ስልጠና ለኮሌጁ መምህራን ከዛሬ ማለትም የካቲት16 /2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናውን የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘውዱ ተሾመና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተገኝተው አስጀምረዋል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት ዶ/ር ዘውዱ ተሾመ ፣አሁን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ የሚለካው ተቋሙ በሚሰራቸው የማህበረሰቡን ህይዎት መሰረት ያደረጉ የምርምር ውጤቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከአሁን በፊት ከነበረው በበለጠ መልኩ ምርምር ላይ ትኩረት አድረጎ እየሰራ እንደሆነና የምርምር ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የስታፍ ስልጠና እየሰጠ የእንደሚገኝ አብራርተዋል፤ ስልጠናው በተግባር የተደገፈ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጁ የምርምርና ህትመት አስተባባሪ ዶ/ር ውዱ ተመስገን፣ስልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው ከ30-40 ለሚሆኑ ስልጠናውን ለመውሰድ ፍላጎት ያሳዩ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ሲሆን ለአራት ተከታታይ ቀናት ይቆያል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተለያዩ አካላት የተሰሩ የጽሁፍ ስራዎችን ሳይንሳዊ አጠቃሎ የሚቀርብበት የአጻጻፍ ክህሎትን ትኩረት አድርጎ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የተለያዩ የምርምር ስራዎችን አንብቦ በመፈተሸ የመምህራንን የምርምር አቅም ለማሳደግ ወሳኝ ነው ሲሉም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት