28ኛው ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 28ኛው የምርምር ጉባኤ “ጥናትና ምርምር በመረጃ ለተደገፈ ዕድገት” / Research for Evidence based Development/ በሚል መሪ ሀሳብ ሚያዝያ 26 ና 27/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሳይንስ አምባ አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው በርካታ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ፣ተመራማሪዎች፣ መምህራን ፣ ተማሪዎች ፤ እንዲሁም ከ20 ያላነሱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፌደራል ሳይንስና ቴክኖሊጅ ሚኒሰቴር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማ/ሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በጥናትና ምርምር አማካኝነት በግብርና፣ በህክምና፣ በትምህርትና በስነ-ልቦና ላይ በርካታ ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸውን ግኝቶች መዳሰሳቸውን ገልጸው “በየአመቱ በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር በመቀየር በኩል በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ ቢሆንም ብዙ ፈታኝ ነገሮች አሉ ፤ለእነዚህ ችግሮች ይህን መሰሉ ጉባዔ መፍትሄ ያፈላልጋል ተብሎ ይታመናል” ብለዋል፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ “ችግር ፈች ምርምሮች ማደረግና ቴክኖሎጅን መፍጠር እንዲሁም ማስራጨት የዩኒቨርሲቲያችን ራእይ ብቻ ሳይሆን የህልውናችንም ጉዳይ ነው፣” በማለት ይህ እውን ይሆን ዘንድ ጥረት ለሚያደርጉ አዲስና ነባር ተማራማሪዎች ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡
በዚህ የምርምር ጉባዔ በሚመለከታቸው ከፍተኛ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ቁልፍ ንግግሮች ተደርገዋል፤ቁልፍ ንግግር ከአደረጉት እንግዶች መካከል የግብርና ኢኮኖሚስት እና አማካሪ ዶ/ር ደምስ ጫንያለው እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ይገኙበታል፡፡
በጉባኤው ላይ በጋራ መድረክ ከቀረቡ የምርምር ስራዎች በተጨማሪ በበርካታ ትይዩ መድረኮች የምርምር ስራዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዷል፡፡ በመጨረሻም አጠቃላይ ውይይት ተካሂዶ የወደፊት የተግባር አቅጣጫ ተመላክቷል ፡፡ አጋጣሚውንም በመጠቀም በዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርሲፕ ማዕረግ ላይ ለደረሱ ፕሮፌሰሮች የእውቅናና የሽልማት ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በየአመቱ የምርምር ጉባኤ መካሄዱ በተለይ በሲኒየርና አዲስ ተመራማሪዎች መካከል ጥሩ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከመርዳቱም በተጨማሪ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች የገለፁ ሲሆን ፤ የምርምርን ሁለንተናዊ ፋይዳ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ጥናትና ምርምር የመስራት ባህልን ለማሳደግ በየአመቱ ጎንደር የኒቨርሲቲ የምርምር ጉባኤ ማካሄዱ ተቋሙ ለአገር ዕድገት የሚያከናውነው ጉልህ ተግባር በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡
በደምሴ ደስታ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት