ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር ካርታና ጥናት ስራ ለመስራት ከአብክመ ማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
በአማራ ክልል በሁለት ወረዳዎች ለሚጠናው የስነ-ምድር ካርታ እና የስነ-ምድር ጥናትና ትንተና ስራ ለመስራት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአብክመ ማዕድን ሀብት ልማት ማ/ ኤጀንሲ ጋር መጋቢት 21/2010 ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
በጃዊና ቋራ ወረዳዎች ሊሰራ ለታሰበው የስነ-ምድር ካርታ ፣ ጥናትና ትንተና ስራ የተለያዩ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች ተወዳድረው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተሻለ መስፈርት አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት የመግባቢያ ሰነዱን ለመፈራረም የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች ጎንደር ዩኒቨርሲቲንና ኤጀንሲውን በመወከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰኔት አዳራሽ ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8833]
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካ/ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ይህን ጥናት ለመስራት ኃላፊነት ወስዶ መዘጋጀቱን አድንቀው ለስራው መሳካት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናቱን በ2.3 ሚሊየን ብር ለመስራት ውል የወሰደ ሲሆን ስራው በ12 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን የሰነዱ ረቂቅ ያሳያል፡፡ የአብክመ ማዕድን ሀብት ልማት ማ/ ኤጀንሲ ም/ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አሊ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን አሸንፎ ጥናቱን ለመስራት ውል መውሰዱ በክልሉ የማዕድን ሀብት ልየታና ልማት ላይ የሚሰራውን ስራ በሚፈለገው ጊዜና ጥራት ለማግኘት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአብክመ ማዕድን ሀብት ልማት ማ/ ኤጀንሲ የማዕድን ፍለጋ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አሰፋ እንደገለጹትም በዋናነት ጥናቱ የሚያተኩረው የስነ-ምድር ካርታውን በ50 ሺ ስኬል/መስፈርት ላይ በማስቀመጥ ዋና ዋና የማዕድናት መገኛ ቦታዎችን ማሳየት እና አጠቃላይ ትንተና መስጠት ነው፡፡ ከስኬሉ ስፋት አንጻርም ሲታይ ይህ የስነ-ምድር ካርታ ስራ በሀገሪቱ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጅ መምህራንና ተመራማሪዎችም በበኩላቸው የተሰጣቸው ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን የመስራት ልምድና እውቀቱ ስላላቸው ስራውን በብቃት ማከናወን እንደሚችሉ በውል ስምምነቱ ላይ ገልጸዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት