ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርናዉ ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር ምክክር አካሄደ
በግብርናዉ ዘርፍ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ክልልና ከስሜን ጎንደር ዞን ሴክተር መስሪያቤቶች ከመጡ የአጋር አካላት ጋር በዩኒቨርሲቲዉ ማኔጅመንት አዳራሽ ሚያዚያ 18/2008 ዓ.ም ምክክር አካሄደ፡፡
ዶ/ር ታከለ ታደሰ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕረዝዳንት በዩኒቨርሲቲው ስም በእንኳን ደህና መጣቹሁ መልክታቸዉ የስ/ጎንደር ዞን ከግብርና ጋር የተያያዙ ችግሮቹን ለመፍታት አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችንና አሰራሮችን ለመጠቀም የሚያስችል የትኩረት አቅጣጫወችንና ግቦችን በማስቀመጥና እንዲተገበሩ በማድረግ የዞኑን ማህበረሰብ ከድህነት እንዲላቀቅ ማስቻል የዉይይቱ ዋና አላማ መሆኑን አዉስተው ዩኒቨርሲቲዉ ከአሁን በፊት እንደሚያደርገዉ ይህን ግብ ለማሳካት የበኩላቸዉን ድርሻ ለሚወጡ ማናቸዉም አይነት ፕሮጅክቶች እገዛ ለማደረግ ቁርጠኝነቱ ያለዉ መሆኑን በመግለጽ ዉይይቱን ከፍተዋል፡፡
በእለቱ ለዉይይት የሚሆኑ ጠቅለል ያሉ እንቅስቃሴን የሚያሳዩ አምስት ጥናታዊ ሪፖርቶች በተለያዩ የተቋም ሀላፊወችና ተወካዮች ቀርበዋል፡፡ በመጀመሪያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ዲን አቶ ሲሳይ የኋላ ስለኮሌጁ አጠቃላይ መዋቅራዊ አደረጃጀት ካቀረቡ በኋላ በአንደኛዉ ስትራቴጅክ ዕቅድ ኮሌጁ ያከናወናቸዉ ስራወችን በዝርዝር በማሳየትና የታዩ ድክመቶችን በሁለተኛዉ ስትራቴጅክ ዕቅድ እንዳይደገሙ ለማድረግ ጠንክረዉ አየሰሩ መሆናቸዉን ገልጸዋል ፡፡ ዶ/ር አቸነፍ መላኩ የእንሰሳት ህክምና ፋካሊቲ ዲን በተመሳሳይ ስለ ፋካሊቲው አደረጃጀትና እየተከናወኑ ያሉ ስራወችን እንዲሁም ወደፊት የበለጠ ዉጤታማ ለመሆን ይበጃል ያሉትን ዝክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ አቶ ዮሃንስ ተስፋየ የስሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ም/ሀላፊ ዞኑ በግብርናዉ ዘርፍ ዉጤታማ እንዳይሆን ማነቆ ናቸዉ ያሏቸዉን ከአብራሩ በኋላ መምሪያዉ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከአጋር አካላት ዉጤታማ ለመሆን ይሻል ያሉትን እገዛዎች ጠቁመዋል፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ሀላፊ የሆኑት አቶ ፀዳሉ ጀንበሬ ሌላው ሪፖርት አቅራቢ ሲሆኑ ስለ ምርምር ማዕከሉ አመሰራረት፣ አደረጃጀትና ማዕከሉ እያከናወናቸው ስላሉ አንኳር ተግባራት አብራርተዋል፡፡ አቶ መሴ አሰፋ የአማራ ክልል ደን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሀላፊ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ ወደ እንደስትሪው በመሸጋገር የህዝቡን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንዴት እንደሚቻል በማህበረሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ ሀገራዊ የደን ልማትን ለአብነት በማሳየት በተመሳሳይ የስሜን ጎንደር ዞን ደኖችን በመንከባክብና መልሶ በማልማት ከዘርፉ እንዴት መጠቀም እንደሚችል የተጠኑ ጥናቶችን መሰረት በማደረግ አስረድተዋል፡፡
የቀረቡትን ሪፖርቶችና ጥናቶች መሰረት በማድረግ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከመድረክ ቀርበዋል፡፡ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ የስሜን ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አብሮ የመስራት ፍላጎት በማሳየቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸዉን ከገለጹ በኋላ በዞኑ ያሉ ደኖችን በማልማትና ሀገር በቀል ዛፎችን በጥናትና ምርምር እንዲባዙ ቢደረግ መልካም ነዉ ብለዋል፡፡ አቶ ሽታሁን ሙሉ ከክልል እንሰሳት ሀብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ፕሮግራሙ በመዘጋጀቱ ደስተኛ መሆናቸዉን ገልጸዉ ነገር ግን የተነሱት መልካም ነገሮች ሳይተገበሩ የመድረክ ግብዐት ብቻ ሁነዉ እንዳይቀሩ ስጋታቸዉን አስቀምጠዋል፡፡
ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ የዩኒቨርሲቲዉ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን በተዘጋጀዉ የምክክር መድረክ ደስተኛ መሆናቸዉን ገልጸዉ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በሚታዩ ችግሮች ላይ ጥናት ከመደረጉ በፊት የትኩረት አቅጣጫወችን (thematic areas) በመለየት በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸዉና በአሁኑ ወቅት የሚሰሩ ምርምሮችም ወቅታዊ ችግሮችን የሚፈቱ መሆን እንዳለባቻዉ አሳስበዋል፡፡
በመቀጠል ዉይይቱን ሲመሩ የነበሩት የጎንደር ዩኒቨረርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አግልግሎት ምክትል ፕረዝዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ መጋቢያዉ ጣሳዉ ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት የጥናትና ምርምር ትኩረት አቅጣጫወች ሲለዩና የትግበራ እቅዳቸዉ ሲታቀድ ምርትና ምርታማነትን የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸዉና ለተግባራዊነታቸዉም ማህበረሰቡን ከድህነት ማዉጣት የሚያስችሉ ተስማሚ ቴክኖሎጅዎችን በትክክል መጠቀም እንደሚገባ በአፅንኦት ገልጸዋለል፡፡ በመጨረሻም በስሜን ጎንደር ዞን በግብርናዉ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ለማድርግ ያመች ዘንድ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ከሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያና ምርምር ማዕከል፣ ከጎንደር ከተማ ግብርና ጽ/ቤትና ምርምር ማዕከል እንዲሁም ከስሜን ብሄራዊ ፓርክ ልማት የተወከሉ የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስነዋል፡፡ የዉይይት መድረኩ ተቀራርቦ በመስራት በኩል ልዩ ድርሻ እንዳለዉ በመግለጽ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የየራሱን ተልዕኮ እንዲዎስድ በማሳሰብ ዉይይቱን አጠናቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አምሳሉ ግዛቸው
አርታኢ ፡ ደምሴ ደስታ