የ3ኛ አመት የአካባቢና ሙያ ደህንነት/Environmental and Occupational Health/ ተማሪዎቸ የማህበረሰቡን ጤና መሰረት ያደረገ የተግባር ትምህርት እያከናወኑ መሆናቸው ተገለጸ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በማህበረሰቡ ውስጥ በመግባት በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ የማህበረሰብ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ የአካባቢና ሙያ ደህንነት /Environmental and Occupational Health / ት/ክፍል ተማሪዎች የተለያዩ በሽታዎችን ቅድመ መከላከል መሰረት ያደረገ ተግባር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እያከነወኑ መሆኑን ነው የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ አካ/ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ የገለጹት፡፡ ዶ/ር አስማማው አያይዘውም ትምህርት ቤቶች እንደዋና የኮቪድ-19 ማስተላለፊያ ስለሚቆጠሩ ተማሪዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ተማሪዎች ለሚያደርጉት የጤንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍና የተግባር ትምህርት እገዛ የሚያደርገው “ናላ ፋውንዴሽን”/NALA Foundation/ የተሰኘ ፕሮጀክት መሆኑን የገለፁት የኮሌጁ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ እና የ”ናላ ፋውንዴሽን” የጎንደር ቅርጫፍ ማኔጀር ዶ/ር መኩሪያው አለማየሁ፣ደንቢያ አካባቢ ለሚገኙ የአምስት ት/ቤት ተማሪዎች ከኮቪድ -19 ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችሉ ከ600 በላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል/ማስክ/ በዛሬው እለት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ 420 ሊትር የሚይዙ የእጅ መታጠቢያ ታንከሮች እና ሳሙና በቅርቡ ለነዚህ ት/ቤቶች ለማድረስም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጤና ተማሪዎቹ በተጠቀሱት ት/ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች በኮቪድ -19 እና በተዘነጉ የትሮፒካል በሽታዎች ላይ በፕሮግራም የታገዘ የጤና ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውንም ዶ/ር መኩሪያው ገልጸዋል፡፡
ይህ ተግባር የአካባቢና ሙያ ደህንነት ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በህ/ሰቡ ውስጥ በመግባት በተግባር የሚተረጉሙበት ፕሮግራም ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ ት/ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ራሳቸውን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲጠብቁ ግንዛቤ ለመፍጥር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስተባባሪው አክለው አብራርተዋል፡፡