የ ጃውስ ሶፍት ዌር” ስልጠና ለ አይ.ሲ.ቲ” መምህራን በደባርቅ ማዕከል እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስነ-ትምህርት ኮሌጅ ለ2ኛ ደ/ት/ቤት አይ.ሲ.ቲ መምህራን የ”ጃውስ ሶፍት ዌር” የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ስልጠና ከየካቲት 18/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በደባርቅ ማዕከል እየሰጠ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስነ-ትምህርት ኮሌጅ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መምህራንን ስለጃውስ ሶፍት ዌር በማሰልጠን አይነ-ስውራን ተማሪዎችን ለመርዳት በደባርቅ ከተማ እየሰጠ ያለው ስልጠናም የዚህ ማህበረሰብ አገልግሎት አካል ነው፡፡ የጃውስ ሶፍት ዌር ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በስ/ጎንደር ዞን ውስጥ ባሉት ሰባት ወረዳዎች ለተወጣጡ 30 የሁለተኛ ደረጀ ት/ቤት የአይ.ሲ.ቲ መምህራን ነው፡፡ በስልጠናው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ኦፊሰር አቶ እንግዱ ገ/ዋህድ እና ስልጠናን በትብብር የሚሰጡት የስነ-ትምህርት ኮሌጅና ኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ መምህራን ተገኝተዋል፡፡

ዋናው የስልጠናው አላማ የመምህራንን አቅም በማጎልበት አይነ-ስውራን ተማሪዎች የጃውስ ሶፍት ዌርን በመጠቀም አይ.ሲ.ቲን በአካቶ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ አብረው ማስተማር እንዲችሉ ለማገዝ እንደሆነ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስነ-ትምህርት ኮሌጅ የጎልማሶች ትምህርትና ማህበረሰብ ልማት ትም/ክፍል ሀላፊና የስልጠናው አስተባባሪ መ/ር ሳሙኤል ዝናቡ ገልጸውልናል፡፡ ከአሁን በፊት ለእነ-ስውራን ተማሪዎች ስልጠናው ሲሰጥ መቆየቱን ያስታወሱት መ/ር ሳሙኤል፣ “የትምህርት አሰጣጡ ዘላቂነት እንዲኖረውና ለበርካታ ተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ መምህራንን ማሰልጠን አስፈላጊ ሆኖ በመገነቱ ይህ ስልጠና ለመምህራን ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሰጠ ነው” ፣ሊሉም ተናግረዋል ፡፡

አይነ-ስውራን ተማሪዎች እንደ አይናማ ተማሪዎች እኩል መማር እንዲችሉ የሚያግዝ በመሆኑ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑንም የስልጠናው ተሳታፊ መምህራን ተናግረዋል፡፡ አይነ-ስውራን ተማሪዎችን የአይሲቲ ትምህርት ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው፤ይህ ስልጠና ግን እነዚህን ተማሪዎች በአካቶ ትምህርት ለማገዝ የሚያስችል አቅምን ይፈጥራል ፣ሲሉ ከደባርቅ መሰናዶ ት/ቤት የስልጠናው ተሳታፊ መ/ር አምባቸው አረጋ ገልጸዋል፡፡ ከአሁን በፊት አይነስውራን ተማሪዎች አይ.ሲ.ቲ የተግባር ክፍለጊዜ ላይ ተለይተው ሳይማሩ ይቀሩ እንደነበርም መምህሩ አስታውሰዋል፡፡

ጃውስ ሶፈተ ዌር አይነ-ስውራን ኮምፒዩተርን በተግባር እንዲጠቀሙ የሚያስችል መተግበሪያ ነው፡፡
የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት