የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ
በዓለማችን እንዲሁም በሀገራችን በተከሰተው የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 ዓ.ም የሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠውን ትምህርት ለማስቀጠል ውድ ልጆቹን በፍቅር ተቀብሎ በእንክብካቤ ለማስተማር በቂ ቅድመ ዝግጅቱ አድርጎ ተማሪዎቹን ዛሬና ነገ (ታህሳስ 3 እና 4/2013 ዓ.ም) በመቀበል ላይ ይገኛል፡፡ ተማሪዎችም በናፍቆትና በጉጉት ሲጠብቁት ወደ ነበረው የትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ከሀጋራችን አራቱም አቅጣጫዎች በመምጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አማራርና መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ “ውድ ተማሪዎቻችንን እንኳን ወደ ሁለተኛ ቤታችሁ ወደ አንጋፋውና የሰላሙ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰላም መጣችሁ::” ይላል፡፡
በቆይታችሁ ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እራሳችሁን ለመከላከል ሙቀታችሁን መለካት፣ አካላዊ እርቀታችሁን መጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግና እጃችሁን በየጊዜው መታጠብ ይኖርባችኋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በዩኒቨርሲቲው በሁሉም ግቢዎች የተዘጋጁ ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑ በእግር ብቻ የሚሰሩ የእጅ መታጠቢያዎች የተዘጋጁ በመሆኑ እነሱን በአግባቡ በመጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡
ውድ ተማሪዎቻችን እርስ በርሳቸሁ በመከባበርና በመቻቻል ሰላማችሁንና ደህንነታችሁን አስጠብቃችሁ የመጣችሁበትን ዓለማ በስኬት ለማጠናቀቅ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድትወጡ ከወዲሁ እናሳስባለን፡፡
እንግዳን በፍቅርና በእንክብካቤ መቀበል ባህሉ የሆነው የጥንታዊቷና የታሪካዊቷ የጎንደር ከተማና የአካባቢው ማህበረሰብም እንደተለመደው ልጆቻችሁን በፍቅርና በእንክብካቤ እንድትቀበሏቸው ስንል ቤተሰባዊ መልዕክት ለጎንደር ከተማና ለአካባቢው ማህበረሰብ እናስተላልፋለን፡፡
******************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 3/2013 ዓ.ም



