የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘላቂ የሆነ ሰላምን ለማስፈን ውይይት አካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ደህንነት በማስጠበቅ ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር ተግባራት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከጎንደር ከተማ የተለያዩ የፀጥታ አካላት( የመከላከያ ሰራዊት፣ የልዩ ሀይልና የፖሊስ መሪዎች)፣ የክልሉ የሰላምና ደህንነት ቢሮና የክልሉ ፖሊስ ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣ የአገር ሸማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የወጣት አደረጃጀቶች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አፀደወይን ከዚህ ቀደም በተማሪዎች ቅበላ ወቅት ይህ የሰላም አደረጃጀት ለዩኒቨርሲቲው ሰላም መስፈን ከፍተኛ የሆነ እገዛ ማድረጉን አንስተው የነበረው መደጋገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ለመስራት ውይይት መደረጉ አስፈላጊ መሆኑንና ለትንኮሳ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ፈጥኖ ለማስተካከል የሁሉንም እርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በመጨረሻም የጎንደርሰ ዩኒቨርሲቲን ሰላም ለማስጠበቅ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም በአሁኑ ሰዓት ፍጹም ሰላምና የተረጋጋ ነው።
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት