የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሂውማን ብሪጅ ጋር የስምምነት ውል ተፈራረመ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሂውማን ብሪጅ ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር የ20 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የሆስፒታል ዕቃዎች የድጋፍ ስምምነት ውል በላንድ ማርክ ሆቴል ሰኔ 28/2008 ዓ.ም ተፈራረመ፡፡
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የሂዩማን ብሪጅ ኃላፊ አቶ አዳሙ አንለይ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አብርሃ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ፣ የዞን ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም የአምስቱ የሰሜን ጎንደር ሆስፒታሎች ስራ አስኪያጆች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የጤናውን አገልግሎት በዓይነት፣ በጥራትና በሽፋን ለማሻሻል በሰሜን ጎንደር ለሚገኙ አምስት አዳዲስና ነባር ሆስፒታሎች የህሙማን አልጋዎች፣ የማዋለጃ ክፍል ዕቃዎች፣ የጥርስ ህክምና መሳሪያዎች፣ አልትራሳውንድ፣ ARG እና መሰል የህክምና መስጫ መሳሪያዎችን መቀመጫውን ስዊድን ሀገር ካደረገው ሂዩማን ብሪጅ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የድጋፍ የውል ስምምነት ፊርማ ተፈራርሟል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በእለቱ ባደረጉት ንግግር ሂዩማን ብሪጅ ከአሁን በፊት 4 ኮንቴነር የህክምና መሳሪያዎችን ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸው ኮንቴነሮች ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ከወደብ በማንሳትና ከጉምሩክ በማምጣት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ድርሻውን እንደተወጣ ገልፀው ነገር ግን በአሁኑ የውል ስምምነት ኮንቲነሮችን እራሱ ሂዩማን ብሪጅ ከወደብ እስከ ዩኒቨርሲቲው እንደሚያደርስ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ ያገኛቸውን እቃዎች በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡና በተገቢው መንገድ ስለሚገለገልባቸው ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ግንኙነት ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ መሰረት ሆኗል ብለዋል አቶ አዳሙ አንለይ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ 200 ቴክኒሻኖችን በቀጣይ ዓመት ለማሰልጠን በዝግጀት ላይ እንደሚገኝም አቶ አዳሙ አንለይ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰለሞን አብርሃ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ይህ የድጋፍ ስምምነት ለሆስፒታሎች አጋዥነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀው የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ካለው የታካሚ የፍሰት ቁጥር ብዛት ተፈላጊውን የሪፈራል አገልግሎት እየሰጠ እንዳልነበር ገለጸዉ ከዚህ ድጋፍ በኋላ ግን አዳዲስ ሆስፒታሎች ይህን የታካሚ ቁጥር ስለሚጋሩት ቁጥሩ እንደሚቀንስና ተገቢ የሆነ የሪፈራል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አኒሳ በፈቃዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ በበኩላቸዉ በዚህ ዓመት ሂዩማን ብሪጅ ካደረገው የ4 ኮንቴነር የህክምና መሳሪያዎች እርዳታ በተጨማሪ ሆስፒታሉ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የህክምና ዕቃዎችን እንደገዛና በቅርቡ ደግሞ 18 ኮንቴነር የህክምና ዕቃዎች በመግባታቸዉ ችግሩን እንደሚቀርፈው ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ አዳሙ አንለይ እቃዎቹ ለአምስቱ ሆስፒታሎች እኩልና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ አንደሚከፋፈል ያላቸዉን ዉስጣዊ መተማመን በዉል ስምምነት ፊረማዉ ላይ ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ይላቅ አለባቸው
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ