የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ
ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ ላለፉት ዘጠኝ አመታት በጎንደር ኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር እና በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ተሰማርተው በርካታ አመርቂ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እኒህ ትጉህ መምህር ያጠኑት plant pathology and applied micro Biology ሲሆን፣ በርካታ የምርምር ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጎልተው የወጡት በባቄላ፣ በሽንብራ፣ በቲማቲም እና በርበሬ በሽታዎች ላይ የሰሯቸው የምርምር ስራዎች ናቸው፡፡ በተለይም በ Biologyical controls አዝዕርቶች በሽታን የሚቋቋሙባቸውን የምርምር ስራቸው በውጤታማነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ሌላው ከዳጉሳ የሚጠመቅ ቢራንም ከዚህ ቀደም እንደሰሩ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደቀረቡ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ነሀሴ 12/2011ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ለእኒህ ተመራማሪ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ ሰጥቷቸዋል፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ 53 የምርምር ስራዎቻቸውን በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ሁለት መፃህፍትንም በተጨማሪ አሳትመዋል፡፡ 1ኛው Effective of environmental pollution and the treatment of micro organisims በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ 2ኛው መጽሐፍ ደግሞ Climate and crop disease በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ ከ130 በላይ የማስተርስና የፒ. ኤች. ዲ ( የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ) ተማሪዎችን የማማከር ስራ ሰርተው አስመርቀዋል፡፡ በእነዚህ ውጤታማ በ2009ዓ/ም እና በ2010ዓ/ም ማለትም ለሁለት ተከታታይ አመታት ምርጥ ተመራማሪ ሆነው ዩኒቨርሲቲው የእውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር በ2010ዓ/ም ባዘጋጀው ውድድር በምርጥ ተመራማሪነት ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በሁለት የምርምር ስራዎች ከኢትዮጵያ የአዕምሮ ንብረት ሀብት የባለቤትነት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዶ/ር ሳሙኤል ሳህሌ ባገኙት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰማንን ደስታ እየገለፅን፣ በመላ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም እንኳን ደስ አለዎት እንላለን ፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት