የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአቶ አምሳሉ ፈለቀ የሙሉ ፕሮፌሰርሽፕ ማዕረግ ሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ህዳር ወር 2008 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ በህብረተሰብ ጤና በመምህርነትና በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፆ ላደረጉት ለአቶ አምሳሉ ፈለቀ የሙሉ ፕሮፌሰርሽፕ የአካዳሚክ ማዕረግ ሠጠ፡፡
ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ በሰሜን ጎንደር ዞን በጎንደር ከተማ ፋሲል ግንብ ግቢ ዉስጥ ከአባታቸዉ አስር አለቃ ፈለቀ ደምሴ እና ከእናታቸዉ ወ/ሮ አንጓች እስጢፋኖስ በ1943 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ከ1-3 ክፍል በፃዲቁ ዩሃንስ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እና ከ4-8ኛ ክፍል በአዘዞ ከተማ አፄ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ በአዘዞ ከተማ በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ባለመኖሩ ወደ ጎንደር ከተማ ተመልሰዉ በድሮዉ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ከ9-11 ክፍል የተማሩ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርታቸዉን የጀመሩት በድሮዉ የህዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ 11ኛ ክፍል ስለሚቀበል ለሁለት ዓመታት ከ1958-1959 ዓ.ም በላብራቶሪ ቴክኒሻንነት ትምህርታቸዉን ተከታትለዉ ተመርቀዋል፡፡
ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ ከምረቃ በኋላ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተዘዋዉረዉ ሠርተዋል፡፡ በ1971 ዓ.ም ወደ ጎንደር ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመመለስ በጤና መኮንንነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸዉን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸዉንም በአሜሪካ ሀገር ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ከ1986 – 1987 ዓ.ም ተምረዉ በማስተር ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ተመርቀዋል፡፡
ፕ/ር አምሳሉ ፈለቀ ይህን ከፍተኛዉን የአካዳሚክ ማዕረግ ለማግኘት በምርምር ስራዎች መስክ ከ20 በላይ የምርምር ስራዎችን ከጓደኞቻቸዉ ጋር በመስራት አሳትመዋል፡፡ በካርተር ሴንተር ድጋፍ በርካታ የመማሪያ ማኑዋሎችን ከጓደኞች ጋር በማዘጋጀት ለትምህርት ስራዎች እንዲዉሉ አድርገዋል፡፡ ከፍተኛ ክህሎት ባገኙበት የጤና ስራ አመራር ትምህርት ዘርፍ ከሁለት ፕሮፌሰሮች ጋር በመሆን ያዘጋጁት የመማሪያ ማኑዋሎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሪያነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ ላገኙት ከፍተኛ የአካዳሚክ ማዕረግ ደስታ የተሰማዉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ስም ለፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡