የጎንደር ዩኒቨርሲቲን የመረጃ ግንኙነት ቴክኖሎጂ ፖሊሲ በተመለከተ ሀገር አቀፍ ወርክሾፕ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የዩኒቨርሲቲውን የመረጃ ግንኙነት ቴክኖሎጂ ፖሊሲ (ICT POLICY ) የተመለከተ ወርክሾፕ ታህሳስ 17/2013ዓ/ም ማራኪ ግቢ አልሙኒዬም አዳራሽ አካሄደ፡፡
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ፣ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር መስፍን በላቸው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ለማ ሌሳ፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ተስፋ ተገኝ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ ዲኖች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ ቀደም ሲል የፖሊሲው ሰነድ መነሻ በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች በማዘጋጀት፣ ኮሚቴ በማዋቀር እና በውስጥ ገምጋሚዎች መገምገሙንና ቀደም ብለው የተሰሩ ስራዎችን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው አብራርተዋል፡፡ በመቀጠልም የእለቱ መርሀግብር የፖሊሲ ሰነዱን ለሁለተኛ ጊዜ በውጭ ገምጋሚዎች በማስገምገም ግብአት ለመጨረሻ ጊዜ በማሰባሰብ ትልቅ የዩኒቨርሲቲ የመረጃ ግንኙነት ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ለማዘጋጀት አላማ ያደረገ ወርክሾፕ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር መሰረት በመጨረሻም ይህ ፖሊሲ ወደ ተግባር ሲገባ ማስፈፀሚያ ስልቶችን ለመንደፍ እና ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም በፖሊሲው ላይ ሀሳብ አስተያየታቸው ለመስጠት የተገኙየዘርፉ ባለሙያዎችንና የውጭ ገምጋሚዎች አመስግነዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አመታት በርካታ ውጤቶችን በማስመዝገብ በተለያዩ ተቋማት እውቅና ሲያገኝ እንደቆየ አውስተው ፣ ለዚህ ውጤት ደግሞ አይ ሲ ቲ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዝ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራዕዩን ዕውን ለማድረግ የዚህ ፖሊሲ መዘጋጀት ከፍተኛውን ሚና እንደሚወጣ ያነሱት ዶ/ር አስራት፣ ይህ ፖሊሲ በውጭ ገምጋሚዎች መገምገሙ ስታንዳርዱን የጠበቀ ፖሊሲ እንዲሆን እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የዚህ ፖሊሲ መዘጋጀት ለዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ለአቻ ተቋማት መነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይህን በማድረግ በኩል ከፍተኛውን ሚና ለተወጡ ዶ/ር መሰረት ካሴንና ሙያዊ ግዴታቸውን ለተወጡ ሙያተኞችና ለዝግጅቱ ኮሚቴ አባላትን ያላቸውን አክብሮት በመግለፅ አመስግነዋል፡፡
በመቀጠል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዝግጅት ኮሚቴ አባል በሆኑት በዶ/ር ተስፋሁን መለሰ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአይ ሲ ቲ ፖሊሲ ቀርቦ በውጭ ገምጋሚዎች ማለትም፣ በዶ/ር መስፍን በላቸው፣ በዶ/ር ለማ ሌሳ፣ በዶ/ር ተስፋ ተገኝ በኩል ያደረጉትን ግምገማ አቅርበዋል፡፡ በግምገማው ላይ በተነሱ ነጥቦችና በአጠቃላይ በፖሊሲው ዙሪያ ሰፊ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው በኮሚቴው አባላት ምላሽና ተጨማሪ አስተያየቶች ተሰጥቶ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ስራ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ስራ እንደሆነና የራሱ የሆነ ፖሊሲ እንዲኖረው መደረጉ እንዲሁም ከሀገራዊ ፖሊሲው ጋር አብሮ የተጣጣመ ሆኖ መሰራቱን ያደነቁት ዶ/ር መስፍን በላቸው፣ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚ ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ እርምጃ ሄዷል ብለዋል፡፡ ዶ/ር መስፍን አያይዘውም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ከዚህ ልምድ በመነሳት የራሳቸውን ፖሊሲ ለማዘጋጀት እንደሚረዳቸው በማስታወስ ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡
ወርክሾፑ በታሰበው መንገድ በርካታ ግብአቶች የተሰበሰቡበት እና በቀጣይ ወደ ትግበራ ለመግባት ሁሉም እራሱን በማዘጋጀት የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ በመርሀግብሩ ተጠቁሟል፡፡ ከፍተኛ አመራሩም የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት የገለፀ ሲሆን፣ በተለያዬ መንገድ አሻራቸውን ሰነዱ ላይ ላሳረፉ አካላትም ምስጋና ቀርቧል፡፡
**********************************************************
ሀጋራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኑነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 19/2013 ዓ.ም