የጎርጎራ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት በተመለከተ ከማህበረሰቡ እና ከሚመለከታቸው አስተዳደራዊ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ
የጎርጎራ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት በተመለከተ ከማህበረሰቡ እና ከሚመለከታቸው አስተዳደራዊ አካላት ጋር የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር መምሪያ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተማ ልማት መምሪያ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳደርና ቤቶች ልማት ጽ/ቤት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሰኔ 19/2013 ዓ.ም በጎርጎራ ከተማ ውይይቱ ተካሂዷል፡፡

የዚህ ውይይት አላማ በጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራን የተዘጋጀውን የጎርጎራ እና አካባውን መዋቅራዊ ፕላን ከመፅደቁ በፊት ለህዝቡ ቀርቦ እንዲተች ለማድረግ እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት እና አስተያየት ለመቀበል መሆኑን የዚህ ፕላን ዝግጅት የቴክኒክ ቡድን ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አየልኝ ተበጀ ገልፀዋል፡፡
መዋቅራዊ ፕላኑ ሲዘጋጅ የባህርዳር ከተማን መሪ እቅድ ከሰሩት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቡድን አባላት ጋር የልምድ ልውውጥና የምክክር ስራ መስራቱን እንዲሁም በውሃማ አካላት ዳር የተገነቡ በውጭ ሀገራት ያሉ ከተሞችን ልምድ እና ከተማዋ ታሪካዊ ይዘቷን በጠበቀ መልኩ እንዴት የቱሪስት ከተማ እናድርጋት በሚል ሀገራቀፍ የምክክር መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር ይህንን ስራ በበላይነት እያስተባበሩና እየተከታተሉ ያሉት የዩኒቨርሲቲው የማህበራስብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው ገልፀዋል፡፡ አቶ ሰለሞን አያይዘው የከተማዋን መሪ እቅድ እና የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት እቅድ እንዲናበብና እንዲመጋገብ የማድረግ ስራ እንደተሰራም ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ የተሰራው ስራ አመርቂ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው እና በዚህ ስራ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ምስጋና እንደሚገባቸው ተሳታፊዎች ገልፀው በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ስራ የሚገባበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የወደብ ቦታ፣ የገበያና የጋራጅ ቦታዎች ከከተማው የራቁ በመሆናቸው ቢታሰብበት፣ የገዳማት ሙዚየም ራሱን የቻለ ቢሆን፣ የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳድጉ የመሬት አጠቃቀም ቢኖሩ የሚሉና ሌሎች ሀሳቦች በተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸው መርሀ-ግብሩ ተጠናቋል ፡፡