የዓለም የሴቶች ቀን – ሴቶች በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ
የአለም የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ፆታና ኤች አይቪ ኤድስ ዳይሬክቶሬት እና የዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ከጀርመን የባህል ማዕከል(ጎቴ) ጋር በመተባበር “ሴቶች በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ(Women in Ethiopian Art)” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 1/2010 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም ህንጻ የመሰብሰቢያ አደራሽ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል፡፡
ዶ/ር አምባሳደር ክብርት ገነት ዘውዴ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደ/ር ደሳለኝ መንገሻ ፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የተከበሩ በሪታ ዋግኔር፣ በኢትዮጵያ የቤልጅየም ም/አምባሳደር የተከበሩ ጆሴፍ ኖድትስ፣ የጀርመን የባህል ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጁሊያ ሳትል፣ እንዲሁም እውቅ የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ተጋባዥ እንግዶች በጉባኤው ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8532]
የስርዓተ ፆታና ኤች አይቪ ኤድስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትግስት ጴጥሮስ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው፣ የሚመሩት ቢሮ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ለአብነትም አሉ ወ/ሮ ትግስት ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው ለሚመጡ እንግዳ ሴት ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል፤ በመሆኑም ሴት ተማሪዎች የማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ የሚረዱና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ሊፈቱ የሚያስችሉ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወስዱ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ በምርምርና በማህበረሰብ አገልልሎት ዘርፍም ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በማህበራዊ ኑሮ ተጠቃሚ በማድረግና መብታቸውን ከማስከበር አንጻር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች በዳይሬክቶሬቱ በኩል እንደሚደረግ ወ/ሮ ትግስት ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ደ/ር ደሳለኝ መንገሻ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ በምክክር ጉባዔው የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ሙያተኞች መሳተፋቸው ለጉባኤው መሳካት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በኪነ-ጥበብ ስራዎችና በሚዲያ ተሳትፎ የሴቶች ውክልና አናሳ መሁኑን ጥናቶች ያመለክታሉ ብለዋል፤ በመሆኑም ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት መሰል የውይይት/የክርክር መድረኮች አወንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2006 ዓ.ም የቲያትር ጥበባት ት/ት ክፍል፣ በ2009ዓ.ም የሙዚቃ ት/ት ክፍል እንዲሁም በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ት/ት ክፍል በመክፈት የሀገሪቱን የኪነ-ጥበብ ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ እንዲል ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደ/ር አምባሳደር ገነት ዘውዴ ቁልፍ ንግግር(keynote speech) አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ሴቶችን በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ የሚያደርጉ ባህላዊ አባባሎችና ልምዶችን በስፋት አስቃኝተዋል፡፡ በተቃራኒው ሴቶች ለማህበረሰብና ለሀገር እድገት ያላቸውን ጉልህ ሚና የቀደሙ የሀገራችንን ታሪኮች በማጣቀስ ለጉባኤው ተሳታፊ አብራርተዋል፡፡ ደ/ር አምባሳደር ኪነ -ጥበባት ጤናማና ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብን ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፤ በመሆኑም አሉ የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ትምህርት ተቋማት፣ በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችና የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤቶች የሴቶችን እኩልነትና መብቶች የማጠናከር ዓላማን ለማሳካት በኪነ- ጥበባት በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በምክክር ጉባኤው ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት በመጡ ሙህራንና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ከ10 በላይ ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበዋል፡፡ ጥናታዊ ጽሁፎቹ በስዕል፣ በቲያትር፣ በሙዚቃ፣ በልቦለድ፣ በፊልምና በማስታወቂያ ስራዎች ውስጥ ሴቶች የተሰጣቸውን አወንታዊና አሉታዊ ምስል በሚመለከቱ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑ እንደነበሩ ከቦታው በመገኘት ለማወቅ ችለናል፡፡
አርቲስት ጸደንያ ገ/ማርቆስ ብዙ ውስብስብና ፈታኝ የሆኑ ሂደቶችን አልፋ እንዴት ለስኬት እንደበቃች በሚማርክና ስሜት በተሞላበት አንደበት የህይዎት ልምዷን ለታዳሚያን አካፍላለች፡፡ በተመሳሳይ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ዝግጅት ላይ ለሙዚቃ፣ ለፊልምና ለቲያትር ት/ት ክፍሎች ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ልምዳቸውን እንዲያጋሩ የተጋበዙ እውቅ የኪነ- ጥበብ ሰዎች(አርቲስት ሰርጸ ፍሬ ስብሐት፣ አርቲስት ይገረም ደጀኔ፣ አርቲስት ሚካኤል ሚልዮን፣ አርቲስት ትግስት ግርማና አርቲስት ሸዊት ከበደ) ከስኬት ማማ ላይ ለመውጣት ምክንያት ናቸው ያሏቸውንና ዝነኛ እንዲሆኑ ያስቻሏቸውን ልምዶች እንዲሁም ያስተምራሉ ያሏቸውን የህይዎት ውጣ ውረዶችና ገጠመኞች ለተማሪዎች አጋርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት