የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌደራሊዝምና ህገ-መንግስት ሀሳቦች ላይ ውይይት አካሄዱ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌደራሊዝምና ህገ-መንግስት ሀሳቦች ላይ ግንቦት 9/2013 ዓ.ም በማራኪ አሉምኒየም አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡ በውይይቱ የብልጽግና ፣አብን ፣ነፃነትና እኩልነት፣ አዴሀን፣መኢአድ፣እናት እና ህብር ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ፓርቲዎች ተወካዮች ፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህን ለሀገር የሚጠቅም የውይይት መድረክ ሲያዘጋጅ ከውይይቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚገኝ በማሰብ እንደሆነ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልጸዋል፡፡ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውይይታችሁ ሀሳብን መሰረት በማድረግ ከጥላቻ የወጣ እና ህዝብን ሊጠቅም የሚችል ሀሳብ ታቀርባላችሁ ብለን እናምናለን፣” ሲሉም ዶ/ር ቢኒያም አክለው ገልጸዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወያዮች በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ምሁራን በእለቱ ርዕሶች ዙሪያ ጠቃሚ ምክረ- ሀሳብ የሚያቀርቡ በመሆኑ የፓርቲ ተወካዮች እነዚህን ሀሳቦች በመውሰድ ቢጠቀሙባቸው ለቀጣይ ጉዧቸው አጋዥ እንደሚሆኑም ም/ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

የስትራቴጅና ፖሊሲ ጥናት ማእከል ኃላፊ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ገበየሁ በጋሻው በበኩላቸው ማዕከሉ ገለልተኛና ስትራቴጅክ የሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ እንዲሰራ የተቋቋመ መሆኑን አንስተው በሀገራችን ለሚደረገው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የበኩሉን አስተዋፆኦ ለማድረግ በማሰብ ውይይቱን ማዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም በምርጫ፣ በህዳሴ ግድብና በሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ተጠቁሟል፡፡
