የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ለመምህራን፣ ለቤተ-ሙከራ ባለሙያዎችና ለአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ለመምህራን፣ ለቤተ-ሙከራ ባለሙያዎችና ለአስተዳደር ሰራተኞች በባዮ ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ የካይዘንን የአምስቱን የመ መርሆዎች አተገባበር ( The Implementation of 5s Methods in Biotechnology Laboratories) ዙሪያ በኢንስቲቲዩቱ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ከሰኔ 16-20/2013ዓ/ም የሚቆይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዲን ፕሮፌሰር ነጋ ብርሀን ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ከመለየቱ ጋር በተያያዘ እንደ ኢንስቲቲዩቱ ታቅደው እየተተገበሩ ካሉት መካከል የሰው ሀይል ልማትን ከማሳለጥና ተወዳዳሪ ከማድረግ በተጨማሪ ቤተ ሙከራዎችን ማደራጀትና በግብአት ማሟላት አንዱ እንደሆነ አውስተው ይህ ስልጠናም በሰው ሀይል ብቃት፣ በአደረጃጀት የተሻለና ተወዳዳሪ የሚያደርግ አንድ እርምጃ እንደሆነ ያላቸውን እምነት በንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ ቤተ-ሙከራዎች ከማሰልጠንና ምርምር ከመስራት በተጨማሪ ገቢ በማመንጨት ማህበረሰቡን ማገልገል እንዲችሉ ስልጠና በመስጠት፣ ያለውን ግብአት በአግባቡ መጠቀምና ተጨማሪ መሳሪያዎችን መሟላት እንደሚገባም ፕ/ር ነጋ ብርሀን ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የካይዘን ትግበራን በተመለከተ ለለውጥ ያለን ዝግጁነት፣ የንብረት ብክነት እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል፣ የቤተ-ሙከራ አስፈላጊ ጥንቃቄ፣ በአዲስ የተሰጠ ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል የሞለኪውላር እና የማይክሮ ባዮሎጂ ቤተ-ሙከራዎች አደረጃጀት፣ የቢሮ አደረጃጀት እንዲሁም በሌሎች የስልጠና ርእሶች ዙሪያ በመ/ር መስፍን ፀጋው፣ በመ/ር አራጋው ዘመነ፣ በመ/ር ሰፊነው ጥላሁንና በዶ/ር ታመነ ምልኪሳ ለተከታታይ አምስት ቀናት ስልጠናው እንደሚሰጥ የተቋሙ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መ/ር ታደለ ታምሩ ገልፀዋል፡፡