“የባለድርሻ አካላት ሚና ከምርጭ በፊትና ከምርጫ በኋላ “በሚል ርዕስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገር አቀፍ ውይይት ተካሄደ
ስድተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ የባለድርሻ አካላት ሚናን ከፍ የማድረግ ዓለማን ይዞ በህግ ትምህርት ክፍል የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ ውይይት ግንቦት 13/2013 ዓ.ም. በማራኪ ግቢ ተካሄደ፡፡ በውይይቱ ከፌዴራል፣ከክልል፣ከዞንና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የመጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊወች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌወች፣ ምሁራንና ተማሪወች ተሳትፈዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በመክፈቻ ንግግራቸው “እንደ ሀገር የህዝብ ቅቡልነት ያለው መንግስት ለመመስረት ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ይገባናል፤ ሀገራችን በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየተፈተነች ያለችበት ሁኔታ ላይ ብትሆንም በመተባበርና በመደጋገፍ ኢትዮጵያ የምታሸንፍበትን ምርጫ ማካሄድ አለብን፤ ኢትዮጵያ የምታሸንፈው ምርጫው ሰላማዊ፣ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሲሆን ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም ምዕራባውያን ሀገራችን በራሷ ሃሳብና በራሷ መንገድ የፈለገችውን እንዳትሰራ የሚያደርግና ተላላኪ የሆነ መንግስት እንዲፈጠር የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቁመው ምርጫው ከፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ከግለሰቦች በላይ ለሀገራችን አስፈላጊ መሆኑን ተረድተን በአንድነት ልንታገል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውን ብዙ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው ይህ ምርጫ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን ብዙ ትርጉም ያለው ምርጫ ነው፤ ይህ ምርጫ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር መሠረት የሚጣልበት፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲሆን ከገዥው ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች፣ ከሃይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች)፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከሲቪል ማኅበራት እና ከሁሉም በላይ ከዜጎች የነቃ ተሳትፎና ወሳኝ ሚና መጫዎት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ገብተው ለመፈትፈት የሚፈልጉ ኃይሎችን ልናሳፍራቸው የምንችለው ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ እንዲሆን በማድረግ ነው ብለዋል። በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መጨረስ እንደምንችል ለጠላትም ለወዳጅም ማሳየት ይገባናል ብለዋል፡፡ ይህ የባለድርሻ አካላት ሚናን ከፍ የማድረግ ዓለማን ይዞ የተዘጋጀው ውይይት ለምርጫ ስርዓቱ ፍትሃዊነት ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ያዘጋጀው የህግ ትምህርት ክፍልና ሌሎችም በዚህ የተሳተፉ ክፍሎችን ሁሉ ፕሬዚዳንቱ አመስግነዋል። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው ሰላምና ደህንነታችን የሚጋፉ የውጭና የሀገር ውስጥ ችግር ፈጣሪዎችን የምናሳፍረው ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ ስናከናውን ብቻ በመሆኑ ሁላችንም ለሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ መዘጋጀት አለብንም ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከክልከላና ከጫና ውጭ ሁኖ የወደደውንና የፈለገውን መምረጥ ሲቻል ነፃነት አለ ብሎ መናገር እንደሚቻል ገልፀው ይህ ነጻነት ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ እኩል ዕድል መኖርን የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል። ዶ/ር ዳኛቸው እንደ ሀገር የሥልጣን ተቀባይነት እንዴት ይመጣል? መሪነትን ለመጨበጥ ምን አይነት መስፈርት ያስፈልጋል? በሚሉት ሃሳቦች ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል።