የሸማች ህብረት ስራ ማህበርን ይበልጥ የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሸቀጦችን ከሌሎች ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በመግዛት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ማህበሩ ሰራተኞች ያለባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ እንዲችሉና በስራቸው ላይ ተረጋግተው እንዲሰሩ ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ተጀምሮ የነበረውን የዩኒቨርሲቲው የሰራተኞች የሸማች ህብረት ስራ ማህበርን እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናከር ማድረግ ዓላማው ያደረገ ውይይት (በዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት አነሳሽነት) ዛሬ ግንቦት 6/2013 ዓ.ም በሴኔት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደ ወይን፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ዘርፉ አቦሀይ፣ የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዳርጌ፣ የዩኒቨርሰቲው የቁጥጥር አካላት፣ የዩኒቨርሰቲው ሸማቾች ማህበር እንዲሁም የጎንደር ከተማ ህብርት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽ/ቤት ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሊቀ መንበር በአቶ ጋሻው በሪሁን የማህበሩ የስራ አፈጻጸም (ከሀምሌ 25/2011 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 25/2013 ዓ.ም) ቀርቧል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግም ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻ ለወደፊት ምን መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጦ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
