የስነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ አደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል የ2013 ተመራቂ ተማሪዎችን በማስተባበር የሰበሰበውን አልባሳትና ገንዘብ ለካለን ብናካፍል የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሰኔ 06/2013 ዓ.ም ድጋፍ አደረገ፡፡
የስነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ጎሹ ኔንቆ፣ የትምህርት ክፍሉን የ2013 ተመራቂ ተማሪዎች በማስተባበር የተለያዩ አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያዎች እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ 18,220 ብር (አስራ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሀያ ብር) መሰብሰቡን ገልጸው በእለቱ ለበጎ አድራት ማህበሩ ተበርክቷል ብለዋል፡፡

“ከዚህ ቀደም በተማሪዎቻችን ቁጥር እና በሆስፒታል ካለን የአዕምሮ ሕክምና ክፍሎች አለመመጣጠን የተነሳ ተማሪዎቻችንን ወደ አዲስ አበባ ቅዱስ አማኑኤል ሆስፒታል ለትምህርት ስንልክ” ነበር ያሉት መምህር ጎሹ፣ ትምህርት ክፍሉ ማህበሩን በበጎ ፍቃደኛ ሠራተኞችና ተማሪዎች ከማገዝ በተጨማሪ ማዕከሉ የተለያዩ የአዕምሮ ሕሙማን ስለሚገኙበት እንደ አንድ የተግባር መማሪያ ቦታ በማድረግ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ከመምህራን ጋር በመመደብ ተግባራዊ የአእምሮ ህክምናም እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ትምህርት ክፍሉ ለጎንደር ካለን ብናካፍል የአዕምሮ ሕሙማን እና አረጋውያን መርጃ ማዕከል እንዲሁም ለጯሂት አቡነ-ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን ማህበር ቋሚ የሕክምናና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ በሚመለከተው ተቋማዊ አካልና በማህበራቱ መካከል የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ (MOU) ለመፈራረም እንቅስቃሴ ጀምረናል ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡