የሳንባ ምች በሽታን ጤና ኬላዎች ላይ ማከም እንደሚቻል ያረጋገጠ የምርምር ውጤት የቀረበበት ወርክሾፕ ተካሄደ
የሳንባ ምች በሽታን ጤና ኬላዎች ላይ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በአፍ በሚዋጥ አሞክሳስሊን ከ5 አመት በታች የሆኑ ህፃናት ማከም እንደሚቻል ያረጋገጠ የጥናት ውጤት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመረማሪዎች የቀረበበት ወርክሾፕ ጎንደር ኃይሌ ገብረስላሴ ሪዞርት ህዳር 26-27/2012 ዓ/ም ተካሄደ፡፡
በወርክሾፑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደ ወይን፣ ዶ/ር መሰረት ዘላለም ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዶ/ር አበባው ገበየሁ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋሻው አንዳርጌ፣ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ፣ የጥናት ቡድኑ አባላት፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

ይህ “Enhanced community case management to increase access to pneumonia treatment ” የሚል ጥናት በሀገር ደረጃ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከ2007ዓ/ም ጀምሮ በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ በወገራ፣ በዳባት፣ በደባርቅ እና በጃናሞራ ወረዳዎች በሚገኙ 20 ቀበሌዎች ስር በሚገኙ የጤና ኬላዎች ላይ የተሰራ መሆኑ በወርክሾፑ ተገልጿል፡፡ ጥናቱ በዋነኝነት ከ5 አመት በታች ያሉ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ አላማ ያደረገ እንደሆነ እና ለህፃናት ሞት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን የሳንባ ምች በሽታ ጤና ኬላ ላይ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ማከም እንደሚቻል ያረጋገጠ ጥናት እንደነበር የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ዘመነ ጥጋቡ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ዘመነ አያይዘውም ከጥናት ቡድኑ አባላት እና ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተጨማሪ አጋዥ የሆኑ ባለሙያዎችን ማለትም፣ የጤና ቀስቃሾችን፣ ሱፐርቫይዘሮችን እንዲሁም ውጤት ተከታታይ ባለሙያዎችን ማሳተፋቸው ለውጤታማነቱ የነበረውን አስተዋዕፆ ጠቁመዋል፡፡

በጥናት ቡድኑ አባላት፣ በዶ/ር ዘመነ ጥጋቡ የጥናቱ ውጤት የቀረበ ሲሆን፣ በዶ/ር አለማየሁ ተክሉ ደግሞ The impact of Health promoters on enrollment of cases and other health services የሚል ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ የቀረበውን የጥናት ውጤት መነሻ በማድረግ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ጥናቱ እንደ ሀገር የመጀመሪያ ሆኖ ውጤት ላይ በመድረሱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ወደፊት ሰፊ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የጥናቱ ውጤት መቅረብ እንደሚገባው ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት