የማህፀንና ተያያዥ አካላት የጡንቻ ችግሮችን መከላከል በተመለከተ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስፔ/ሆስፒታል የሴቶችና ቤተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የማህፀንና ተያያዥ የጡንቻ ችግሮችን መከላከል /Prevention and Management of Pelvic Floor Dysfunction/ በተመለከተ ከምዕራብና ከምስራቅ ደንቢያ ከተለያዩ የጤና ተቋማት ለመጡ የጤና ባለሙያወችና ለቀበሌ የጤና ልማት ተወካይ ሴቶች በቆላድባ ከተማ መጋቢት 3 እና 4/2013 ዓ.ም በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ::

ስልጠናው በዋናነት የሚያተኩረው የማህፀንና ተያያዥ አካል ጡንቻ ችግሮች: የማህፀን መውጣት :የሽንትና ሰገራ መቆጣጠር አለመቻል መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ አጠ/ስ/ሆስፒታል በሚድዋይፈሪ ት/ቤት ሴቶችና የቤተሰብ ጤና ትም/ክፍል ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ በላይነህ አያናው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲከሰቱ እናቶች በሚስጥር ይዘውት ከባድ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ስለሚቆዩና በአገራችንም ያለው የማህፀንና ተያያዥ አካል ጡንቻ ችግሮች ቀዶ ህክምና አገልግሎት ውስን በመሆኑ ሁኔታውን ውስብስብና ፈታኝ እንደሚያደርገው አቶ በላይነህ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይህ ስልጠና መሰጠቱ ህብረተሰቡ በእነዚህ ችግሮች ላይ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት አስቀድሞ እንዲከላከል ለማስቻል ፣ችግሩ ሲከሰትም ታክመው መዳን እንደሚቻሉ ለማስገንዘብ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ እናቶችን በአግባቡ እንዲረዱ ለማስቻል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስተባባሪው ተናግረዋል::