ዓለምአቀፋዊ እና ሀገራዊ የቅርስ ህጎች ለዘላቂ ዓለምአቀፋዊ ቅርሶች አስተዳደር” በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ
የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል በዓለምአቀፋዊ እና ሀገራዊ የቅርስ ህጎች እና በዘላቂ የዓለምአቀፋዊ የቅርሶች አስተዳደር ዙሪያ ከሰሜን ጎንደር ከተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ 40 ለሚሆኑ የባህል እና ቱሪዝም አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከየካቲት 13 -14/2012 ዓ.ም በደባርቅ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።

የኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር መስፍን ደስየ “ዩኒቨርሲቲያችን በቅርስ እና በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ ስራ ከሚሰራባቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ጎንደር ነው። በመሆኑም ዓለምአቀፍ እና ሀገራዊ ህጎችን ለእናንተ በማስተዋወቅ ቅርሶችን መጠበቅ እና በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችላችሁን አቅም እንድታዳብሩ ይረዳችኋል የሚል እምነት አለን” ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል።

የስልጠናው ዋና አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሸጋለም ፍቃዱ “ተቋማዊ መዋቅር፣ ሀብት እና ህጎች መኖር መሰረታዊ የቅርስ አስተዳደር ንድፍ ሃሳቦች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎችን ማወቅ ቅርስን ለሚያስተዳደሩ አካላት አስፈላጊ ነው። ቅርሶችን በአግባቡ ለማስተዳደር እና ቅርሶች ላይ መደረግ የሌለባቸውን ነገሮች ተገንዝበን የቅርስ ሀብታችን በአግባቡ ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ የዚህ አይነት ስልጠና ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ጌትነት መርዕድ የቅርስ ምንነትና የቅርስ አስተዳደር ንድፈ ሃሳቦች ላይ፣ አቶ ማርሸት ግርማይ የባህላዊ የቅርስ አስተዳደር ስልቶች ላይ እና አቶ ጌታቸው አለምነህ ዓለምአቀፋዊ የቅርስ ህጎች ለዘላቂ የቅርስ አስተዳደር ያለቸውን ፋይዳ ስልጠና ሰጥተዋል። በተመሳሳይ አቶ ሸጋለም ፍቃዱ የኢትዮጵያ የቅርስ ህጎች ለዘላቂ የቅርሶች አስተዳደር ያብራሩ ሲሆን አቶ ታሪኩ ታደለ የኢትዮጵያ የቅርስ ህጎች ሲጣሱ የሚከተሉ ቅጣቶችን አስረድተዋል።

በጨረሻም ይህው ስላጠና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚሰሩ የባህል እና ቱሪዝም አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና የሃይማኖት አባቶች በቀጣይ የካቲት 28-29/ 2012 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚሰጥ የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ሸጋለም ገልፀዋል።
//ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር//