አዲስ ሒዎት የበጎ አድራጎት ማህበር የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስር ከተቋቋሙ የተለያዩ በጎ አድራጎት ማህበራት መካከል አንዱ የሆነዉ አዲስ ሂዎት የበጎ አድራጎት ማህበር ከተለያዩ ቦታዎች ከመጡ መስራችና አዳዲስ አባላት ጋር የዩኒቨርሲዉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙነት በዩኒቨርሲቲዉ ቅጥር ግቢ በተለያዩ ቦታዎች ሚያዚያ 29- 30/2008 ዓ.ም ማህበሩ የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ፡፡
የመጀመሪያዉ ዝግጅት የዳቦ ቆረሳና የእግር ጉዞ ስነ ስርዓት ሲሆን ዝግጅቱን ለማስጀመር የዩንቨርሲቲዉ የአስተዳደር ምክትል ፕረዝዳንት አቶ ሰሎሞን አብርሀ፣ የዩንቨርሲቲዉ የተማሪዎች ዲን አቶ አንተነህ ደመቀ እና የዩኒቨርሲቲዉ የአአስተዳደር ምክትል ፕረዝዳንት ረዳት አቶ ዳዊት ዳርጌ ተገኝተዋል፡፡ በመክፈቻ ዝግጅቱ ላይ አቶ ሰሎሞን ማህበሩ እያከናዎናቸዉ ያሉ ስራዎችን በማድነቅና ለወደፊት ከዚህ በበለጠ ተግተዉ በመስራት ማህበሩን በሃገራችን አሉ ከሚባሉ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች አንዱ እንደሚሆን ምኞታቸዉን ገልጸዉ ‘በጎ አድራጎት ለሁሉም’ የሚል ሞፈክር አላማዉ ያደረገዉን የእግር ጉዞ አስጀምረዋል፡፡ የእግር ጉዞዉ በማህበሩ ተወጥኖ ከተሰራዉ ቴወድሮስ ካምፓስ ወጣቶች ማዕከል መነሻ አድርጎ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መድረሻ ያደረገ ነበር፡፡ በጉዞዉ ላይ የተለያዩ ህብረተሰቡን ለበጎ አድራጎት እጁን እንዲዘረጋ የሚያነሳሱ ሞፎክሮችና ህብረ ዝማሬወች አሰምተዋል፡፡
በሚቀጥለዉ ፕሮግራም ላይ ማህበሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴዉን ጥሪ ለተደረገላቸዉ እንግዶች አቅርቧል፡፡ የማህበሩ የቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር ናሆሜ ተሾመ በመጀመሪያ ስለ ማህበሩ አመሰራረት፣ እያከናዎኗቸዉ ስላሉ ተግባራት እና ስለዎደፊት እቅዶቻቸዉ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በመቀጠል ማህበሩ ሊተገብረቸዉ ካቀዳቸዉ ፕሮጀክቶች መካከል ቆሻሻን እንዴት መልሶ መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ ፕሮጀክት በማህበሩ አባል የዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት ሄኖክ ዳኘ ቀርቧል፡፡
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የኪነትና ባህል ማዕከል(ኪባማ) ቡድን ‘የምንዱባን መንደር’ የተሰኘ በጎ አድራጎትን የሚያበረታታ መነባንብና ድራማ አቅርቧል፡፡ የድራማዉን ሀሳብ እንደ መወያያ እርዕስ በመምረጥ ታዳሚዋች ስለ በጎ አድራጎት ያላቸዉን የተለያዩ ሀሳቦች በማንሳት ተወያይተዉባቸዋል፡፡ እንዲሁም ማህበሩ እገዛ በሚያደርግላቸዉ ህጻናት የቀረበዉ ሙዚቃ፣ ግጥም፣ ጥያቄና መልስ ለዝግጅቱ ድምቀት ሁኗል፡፡
የማህበሩ መስራችና የቦርዱ ሰብሳቢ ዶ/ር ደሞዝ ታደሰ ማህበሩ እንደ መመሪያ(principles) የሚከተላቸዉ ነጥቦችን ማለትም ሰዉ ከገንዘብ የበለጠ ሀብት መሆኑን፣ ማህበሩ የራሱን አቅም ተጠቅሞ ገቢ ማመንጨት እንደሚችልና ማህበሩ እየሰራቸዉ ያሉ በጎ ስራወች ለእይታ ሳይሆን ከትክክለኛ የሰባዊነት ስሜት የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከማህበሩ ስኬት በስተጀርባ ምንጊዜም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተለይቷቸዉ እንደማያዉቅና ለዎደፊትም ግንኙነታቸዉ ጠንክሮ እንደሚቀጥል በሙሉ እምነት ተናግረዋል፡፡ ቀጥሎም ዶ/ር ደሞዝ ለማህበሩ ስኬት ከፍተኛዉን ድርሻ ላበረከቱ ግለሰቦች የእዉቅናና የምስጋና ሽልማት አበርክተዋል፡፡
በመጨረሻም ጥሪ ከተደረገላቸዉ እንግዶች መካከል በማህበሩ ሙሉ ድጋፍ ህንድ ሀገር ሂዳ የኩላሊት ህክምና የተደረገላት አርሴማ ካሳሁን በክብር እንግድነት የተገኘች ሲሆን በፕሮግራሙ መሪና የማህበሩ ስራ አስከያጅ መሳፍንት አያሌዉ ጋባዥነት መድረክ ላይ ወጥታ እንደተናገረችዉ ህንድ አገር ደርሳ ከመጣች በኋላ ጤናዋ ሙሉ በሙሉ በመመለሱ ለአዲስ ሂዎት ማህበር አባላት ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡ ነገር ግን በየሳምንቱ ለምርመራ(check up) እና በየወሩ ለምትወስደዉ መዳህኒት እምታወጣዉ ወጭ ከአቅሟ በላይ ስለሆነባት አሁንም የማህበሩና የመሰል በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ግለሰብ እርዳታ እንደምትሻ ገልጻለች፡፡ እኛም በበጎ አድራጎት ላይ መሳተፍ የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡
ዘጋቢ፡ አምሳሉ ግዛቸዉ
አርታኢ፡ ኤልያስ መንበሩ