በጤናው ዘርፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ በጤናው ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር ግንቦት 05/2008 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡
ዶ/ር ታከለ ታደሰ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት
በውይይቱ ላይ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ፣ ከሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ፣ እና ከክልል ጤና በሮ የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ መምህራን እና ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን
የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰ ጥሪያቸውን አክብረው ለመጡ ተወያዮች ምስጋና ሲያቀርቡ እንዳሉት የምክክር መድረኩ ዓላማ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ፣ በሰ/ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ እና በክልሉ ጤና ቢሮ መካከል በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ያሉ ችግሮችን መፈተሸና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት የጋራ ራዕይ እንዲኖርና ዝርዝር እቅዶችን ተዘጋጅተው የሂደት ተፅዕኖ መከታተያ የጊዜ ሰሌዳ ለመዘርጋት ነው ብለዋል፡፡
የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተሟላ መንገድ ለመተግበርና የህዳሴያችን ጉዞ ለማፋጠን፣ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ እና የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ማሻሻል ዋናው ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ የምርምር ስራዎች በማህበረሰቡ ችግርና ፍላጎት ላይ ያልተመሰረቱ፣ማህበረሰቡን ያላሳተፉና የማህበረሰቡን ዕውቀት ያላካተቱ በመሆናቸው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አልተቻለም ነበር ብለዋል ዶ/ር ታከለ ታደሰ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው ከጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር በጋራ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማውጣትና በመለየት በተግባር በመተርጎም እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የእናቶችንና የህፃናትን ሞት መጠን መቀነስ፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋንን ማሻሻል፣ ህዝቡ በህይወት የመኖር የእድሜ ጣሪያ ከፍ ማድረግ እና የህዘቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎች እነዚህንና መሰል ተግባራትን ለመስራት አቅምና እዉቀቱን ተጠቅሞ በጥናትና ምርምር፣ በአቅም ግንባታና መስል ስራዋች በቀጣይ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት ዪኒቨርሲቲዉ አንደሚሰራ ም/ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንዳሉት ከ62 ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲው ሲመሰረት በደንቢያ የወባ ወረርሽኝ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን መግደሉ የመለስተኛ ጤና ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋም እንዲቋቋም መነሻ የሆነው፡፡ ይህ የሚሳየዉ የዩኒቨርሲቲው አመሰራረት የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ሲባል ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ጤና ተቋም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጤና አጠባበቅ ተቋም እንደሆነና የሰው ኃይልን በማፍራት እና በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳበረከተ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 62 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከስራቸዉ በርካታ ስራዎች መካከል በሀገር አቀፍ ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የጤና ባለሙያዎችንና ሀኪሞችን በማፍራት የሚታወቅ ትልልቅ የምርምር ማዕከላት ያሉት አንጋፋ ተቋም አንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የጎንደር ከተማና የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸውን (Thematic areas) አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከተነሱት የትኩረት አቅጣጫዎች ተጨማሪ ከተወያዮች ትኩረት አልተሰጣቸውም ትኩረት ሊሰጣቸዉ ይገባል ብለው ካነሷቸው የትኩረት አቅጣጫ መካከል፡- የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ የሚሰጡትን አገልግሎት በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆኑና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግበት ዘዴ ቢፈጠር፣ አካል ጉዳተኞች ላይ ስራ እየተሰራ አይደለምና ቢሰራ፣ እንደ ጫት ያሉ አደንዛዥ እፆች ተኩረት ተሰጦ ቢሰራ፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ፣ አዕምሮ ጤና ላይ፣ ውሃ እና ሳንቴሽን ላይ፣ ለገጠሩ ማህበረሰብ የንፁ ውሃ አቅርቦት እጥረት ላይ፣ መሰረታዊ የቀዶ ጥገና ጥንቃቄ ሽፋን ላይ እና መሰል የትኩረት አቅጣጫዎችን አንስተው ጥናትና ምርምር ቢደረግባቸው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከክልል ጤና ቢሮ የመጡ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዳሉት ክልሉ ከጎንደር ዪኒቨርሲቲ ሆስፒታል በጋር በመሆን በጤናዉ ዘርፍ 11 የትኩረት አቅጣጫዎችን ነድፎ እየሰራ እነደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህም ቢሆን የጎንደር ከተማና የሰሜን ጎንደር ዞን በጤናው ዘርፍ ዝቅተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ አንጋፋ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ62 ዓመት በፊት TTP(የመስክና ቡደን ስልጠና) የሚሰጥ ተቋም ያለው ዞን እና ከተማ የጤናው ዘርፍ አፈጻጸም ሊወድቅና ዝቅ ሊል አይገባም ነበር የሚሉ ጥያቄ አዘል አስተያየት አንስተዋል ፡፡
ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሰራቸውን ስራዎችና አጠቃላይ ተግባራት ለማሳየት ባቀረቡት ፅሁፋቸው እንደገለፁት ኮሌጁ ከኢትዮጲያ ዉጭ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሌለ BSC in Health Informatics በጎንደር ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ብቻ እንደሚሰጥ፣ በዓይን ህክምና ላይ ከORBIS International አጋር ድርጅት ጋር በጋራ ላለፉት አስራ አራት ዓመታት እየሰሩ እንዳሉና የዐይን ቀዶ ጥገና ወሰኑን በማስፋት በክማክሰኝትና በመራዊ ጤና ጣቢያም እንደሚሰጥ፣ ዩኒቨርሲቲዉ ከCDC አጋር አካል ጋር ባደረገዉ የፕሮጀክት ስምምነት የሪፈራል ሆሰፒታል ማስገንባት አንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ ስምንት ሽህ የሀክምና ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ከተመሰረተ እስከ አሁን ድረስ 20,000 የህክምና ጤና ሙያተኞች ለሃገሪቱ እና ለዓለም እንዳበረከተ ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህሙማን በማከም ትልቁ እንደሆነ ዲኑ አብራርተዋል፡፡ በጎንደር፣ በቆላድባ፣ በዳባት፣ በደባርቅ፣ በአርማጭሆ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በየአመቱ አምሳ ትንንሽ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና በመተግበር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ አድርገዋል ብለዋል ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ለ46705 ህዝብን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚ አድርጓል ይህም በገንዘብ ሲሰላ ግማሽ ሚሊየን ብር እንደሚደርስ ደ/ር ሲሳይ ይፍሩ ገልፀዋል፡፡በአማራ ክልል ሶስት ሺ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ከ10 እስከ 15 ቀናት የክህሎት ስልጠና በየዓመቱ ኮሌጁ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ሁላችንም አላማችንና ተልኳችን ጤናማ ዜጋን በመፍጠር ድሀንትን ማጥፋትና አንዲት ያደገች ሀገር ኢትዮጵያን መገንባት ስለሆነ ዩኒቨርሲቲዉ ከክልሉ፣ ከዞኑና ከጎንደር ከተማ ጋር በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፡፡
ዘጋቢ፡ ይላቅ አለባቸዉ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ሪፖርተር
አርታኢ፡ ደምሴ ደስታ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር