በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአድዋ 125ኛ ዓመት የድል በዓል ተከበረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን እንኳን ለአድዋ 125ኛ ዓመት የድል በዓል አረሳችሁ ካሉ በኋላ የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድል እንዲሁም የመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ቀን በመሆኑ ልንኮራበት ይገባል ፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ከዚህ ድል አንድነትንና ፍቅርን መማር ይገባችኋል በማለት አብራርተዋል ፡፡

በዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ ሁነው ንግግር ያደረጉት ሀገር ወዳዱና የታሪክ ተመራማሪ መምህር ታዬ ቦጋለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ በመሆንዋ ልንኮራባት ይገባል፡፡ ታሪካችን ረዥም ነው ህዝባችን ከፍ ያለ ነው በዚህ ከፍታችን አድዋ ላይ በፍቅርና በአንድነት የመጣብንን ወራሪ ቅስም ሰብረን መመለስ ችለናል በዚህ ዘመን የተፈጠረውን የሀሰት ትርክት የ50 ዓመት ታሪክ በማንጠልጠል ለመለያዬት መጣር ተገቢ አይደለም ፡፡
የዩኒቨረሲቲ ተማሪ ትልቁ መለያው ነገሮችን በምክንያት ማሰብ ነው በስሜት ሳይሆን በስሌት በመሰለኝና በደሳለኝ ሳይሆን በአመክንዮ ማየት መቻል ነው፡፡ አንድ የሚያደርጉንን በርካታ ታሪኮቻችን በማጥናትና በመተንተን የጋራ የሆነ እውነት በመያዝ በአንድነት መጓዝ ይጠበቅባችኋል ፡፡ አድዋ የትናንትና የዛሬን ትውልድ የሚያስተሳስር አንገታችን ቀና አድርገን በዓለም ሁሉ የምንጓዝበት ድላችን ነው ሲሉ አስረድተዋል ፡፡

የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለተጋባዥ እንግዶችና ለዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኞች እንኳን ለአድዋ የድል በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተለያዩ ስነ-ግጥሞችን መጣጥፍና ሙዚቃ ያቀረቡ ሲሆን ጀግኖች አርበኞችም የበዓሉ ድምቀት ነበሩ ፡፡
