በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሰራው የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን- ጎንደር መካነ አዕምሮ ቁ-1 በይፋ ተመረቀ፡፡
በጣና ሀይቅ ላይ በፍጥነት በመስፋፋት የሀይቁን ህልውና አደጋ ላይ የጣለው እምቦጭ የተሰኘው መጤ አረም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሩቱ ዜጎች በስፋት አነጋጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ሁኖ መቀጠሉ ይታወሳል፡፡ ያህንን አስከፊ አረም ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቆርጦ በመነሳት ይበጃሉ የተባሉ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ ተቋሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና እንደ ፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ያሉ ደጋፊ ማህበራትን በማስተባበር በሰው ሀይል አረሙን በማጽዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከማድረግ በተጨማሪ ከ50 ሳ.ሜ. ከሀይቁ ጥልቀት ጀምሮ በውሀ ላይ በመንሳፈፍና በማጨድ አድቅቆ ማስወገድ የሚችል ዘመናዊ ጀልባ መሰል ማሽን /ጎንደር መካነ አዕምሮ ቁ-1 ህዳር 19/2010 ዓ.ም በማስመረቅ የመጀመሪያ የስራ ሙከራ በይፋ አድርጓል፡፡
[widgetkit id=7674]
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የአማራ ክልል የመንግስት ዩኒቨርርሲቲዎች የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የአማራ ክልል ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሰብስበው አጥቃው እና ሌሎች የሚመለከታቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በምረቃው ወቅት ተገኝተዋል፡፡
ይህ ማሽን ከዚህ ሙከራ በመቀጠል አስፈላጊ ጥቃቅን ማሻሻያ ተደርጎበት በቅርብ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ስራ እንደሚጀምር ያላቸውን ሙሉ እምነት የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የቴክኖሎጅ ውጤቶች በሂደት የሚሻሻሉና የሚስተካከሉ በመሆናቸው በእለቱ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ማሽኑን ወደ ስራ ከማስገባት በተጨማሪ ተቋማቸው አረሙን ለማጥፋት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ አረሙን ለማጥፋት የሚችሉ ብሎም አረሙን ለተለያዩ የእንዱስትሪ ውጤቶች ግልጋሎት ላይ እንዲውል የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ የላቭራቶሪ ምርምሮችም በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ መሆናቸውን አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ይህንን የሙከራ ቀን ሁላችንም በናፍቆት ስንጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው ያሉት የአማራ ክልል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሰብስበው አጥቃው ናቸው፡፡ ኮሚሽነሩ ሀገራችን በፍጥነት እንድታድግ በዋናነት የቴክኖሎጂና ሎሎች የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና ድጋፍ ማድረግ ሲቻል መሆኑን በአንክሮ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው እምቦጭን ለማጥፋት የሚያደረገውን ጥረት በማድነቅ መስሪያ ቤታቸው ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ከዩኒቨርሲቲው ጎን እንደሚቆም በሙሉ እምንት ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰለሞን መስፍን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንደስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከማሽኑ ሙከራ በኋላ እንደተናገሩት ማሽኑ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ወርክ ሾፕ ሙሉ በሙሉ እንደተሰራ አውስተዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ማሽኑ አረሙን ወደ ውስጥ በመሳብ/pump/፣ በማጨድና በማድቀቅ ለማስወገድ ዓለማ የተሰራ በመሆኑ ሀርቨስተር/harvester ማሽን እንደሚሉት እና ጎንደር መካነ አዕምሮ ቁጥር-1 የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የጠቆሙ ሲሆን በሰዓት እስከ 50 ኩንታል አረም በማንሳት ማጽዳት እንደሚችልም ገልጸው ሀርቨስተር ማሽኑ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባ አረጋግጠዋል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ምርምሮችም በተቋሙ እንደሚቀጥሉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በመረቃው ወቅት ያነጋገርናቸው አንዳንድ የአማራ ክልል የመንግስት ዩኑቨርሲቲዎች የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፐሬዚዳንቶች ባዩት ነገር መደሰታቸውን እና ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጸውልናል፡፡ ለአብነት ያክል፣ “ከዚህ በፊት በተለያየ መልኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን እየሰራ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ዛሬ በአካል ሲሞከር ሳይ ምርምሮች እንደዚህ ከወረቀት አልፎ በተግባር ውጤታቸው ሲታይ እንዴት ያስደስታል መሰላችሁ፡፡ ባጠቃላይ ያየሁት ነገር ትምህርት ሰጪ እና አስደሳች ነው፡፡ በርቱ! ” በማለት ዶ/ር አልማዝ አፈራ የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት በወቅቱ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
እኛም በማሽኑ ምረቃ ላይ ተገኝተን በተመለከትነው ሁሉ በእጅጉ ደስ ብሎናል፣ ወደፊት ዩኒቨርሲቲያችን በእንቦጭ አረም ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እየተከታተልን የምንዘግብ ይሆናል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት