በዓለም የመጀመሪያ የሆነ ኮንግረንስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ
በዓለም የመጀመሪያ የሆነዉ የጉቴሽን ወይም ቁርዘት የምርምር ኮንፈረንስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ገጠር ትራስፎርሜሽን ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት አቶ ሰለሞን አብርሃ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ እንደገለፁት “በዚህ ወቅት በፈረንሳይ ሃገር ከ200 በላይ የሚሆኑ ሀገራት ስለ አየር ብክለት እና በሰዉ ልጆች ላይ ስለሚያደርሰዉ ችግር እየተወያዩ ባለበት ወቅት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብዙ ያልተነገረለትና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ለአካባቢ ልማት ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያደርገዉን የጉቴሽን ወይም ቁርዘት ኮንፈረንስን ስናካሂድ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፡፡
ዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብም ችግር ፈች የሆኑ መሠረታዊ ጥናቶችን እያከናወነ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነዉ፡፡ ካሉ በኋላ በተለያዩ ሃገራት የመጣችሁ ታዋቂና በሳል ተመራማሪ ሳይንቲስቶች እንኳን ወደ ዩኒቨርሲቲያችን በሠላም መጣችሁ፤ የእናንተ መምጣት በርካታ እዉቀትን፣ ልምድንና ሃሳብን እንድንጋራ ያደርገናል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አቶ ሰለሞን አብርሃ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ንግግር ሲያደርጉ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ የኋላ በበኩላቸዉ “ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከኔዘርላንድ፣ ከእስራኤልና ከጀርመን ሀገር በመጡ ታዋቂ የሆኑ ፕሮፌሰሮች በዓለም የመጀመሪያ የሆነዉን የቁርዘት ኮንፈረንስ እዚህ በማከናወናችን ደስተኞች ነን፡፡
የምርምር ኮንፈረንሱ ዋና ጉዳይ በጉቴሽን ወይንም ቁርዘት ላይ የተሰሩ የምርምር ስራዎች የሚቀርቡበትና ከፍተኛ ልምድ የምናገኝበት ሲሆን ሀገራችን በርካታ ብዝሃ ህይወት ያለበት በመሆኑ በቁርዘት ላይ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎቻችን ወደ ፊት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይሰጣል”፤ ብለዋል፡፡
የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ የኋላ እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሲያደርጉ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር እና የጉቴሽን ኮንግረሱ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ፈጠነ በኮንፈረንሱ ተገኝተዉ እንደገለጡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጉቴሽን ላይ እያካሄደ ያለዉ ኮንፈረንስ በዓለም የመጀመሪያዉ ሲሆን በ17ኛዉ ክፍለ ዘመን ተጀምሮ ለህክምና ተግባራት ይዉል የነበረዉን አሁን ለግብርና ምርምር ስራዎች ለሰዎች፣ ለእንስሳትና ለሰብል ጥቅም ላይ እንዲዉል እየተከናወነ ያለዉ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮንግረሱ ፋና ወጊ ተግባር ነዉ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንጋፋና ዉጤታማ በመሆኑ ይህን ኮንፈረንስ በመጠቀም ሀገራዊ የሆኑ ምርምሮችን እንዲሰሩበት ሊያድርግ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር እና የጉቴሽን ኮንግረሱ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ፈጠነ፡፡
ወጣቱ ተመራማሪ መምህር ዩሃንስ ሞገስ በበኩሉ ቁርዘት ማለት ከተክሎች ቅጠል ዉስጥ የሚወጣ በርካታ አይነት ፕሮቲኖችን የያዘ ጤዛ መሰል ፈሳሽ ሲሆን ብዙ ጊዜ በተክሎች ቅጠል ላይ በጠዋት የሚታይ ነዉ፡፡ ይህ ከዕፅዋት የሚገኘዉ ጠብታ ለበርካታ ምርምሮች በር የከፈተና ብዙ ያልተሰራበት በመሆኑ በዚሁ በቁርዘት ላይ የተደረጉ ጠቃሚ የምርምር ሠነዶች በዚሁ ኮንፈረንስ ይቀርባሉ፡፡ እኛም እዚሁ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላይ የራሳችን ስራ እናቀርባለን፡፡ ከዚህም ከፍተኛ ተሞክሮ በመቅሰም ለሀገር ጠቃሚ የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ማከናወን ያስችለናል በማለት ያስረዳል፡፡
ይህ የጉቴሽን ወይንም ቁርዘት ኮንፈረንስ ከህዳር 23 እስከ ህዳር 25/2008 በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ሲካሄድ በአይነቱ የመጀመሪያ የመጀመሪያ እንደመሆኑ ኮንፈረንሱ ለነባርና አዲስ ተመራማሪዎች የምርምር ፍንጭ የሚሆኑ ሃሳቦች የሚፈልቁበት እንደሆነም ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ