በእስር ቤት ቆይታ ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች የ2ኛ ዙር ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ቢሮ በጎንደርና አካባቢው ለሚገኙ በነጻነት ተጋድሎ ምክንያት በፖለቲካ እስር ቤቶች ለቆዩ፣ ከስራ ተፈናቅለው ለነበሩና ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በአይነቱ ለየት ያለ ስልጠና በማዘጋጀት፣ የመጀሪያ ዙር ማጠናቀቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከታህሳስ 30 እስከ ጥር 4/2012 ዓ.ም የሚቆይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ስልጠና፣ ማለትም በስነ-ልቦና ግንባታ፣ በስራ ፈጠራ፣ ራስን በመምራት ጥበብ፣ በቢዝነስ አሰራር እና እቅድ፣ በህይወት ክህሎት፣ በጊዜ አጠቃቀም እና ተያያዥ ጉዳዮች ለ2ኛ ጊዜ ለሌሎች መሰል ግለሰቦች ስልጠናው መሰጠት ጀምሯል፡፡ ቀጣይ ዙሮች በስልጠናው ላልተሳተፉ ግለሰቦች እንደሚኖሩ መገለጹም ይታወሳል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ ራስን ለመቀየር የሚያግዙ ብዙ ቁምነገሮች ከስልጠናው እንደሚገኝ አስተባባሪው አስታውሰዋል፡፡ ተሳታፊዎች በትኩረት ክትትል እንዲደርጉም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር፣ ማ/ሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ናቸው፡፡ ተሳታፊዎች ትልቅ መስዋዕት በመክፈል፣ አሁን ለታየው ሀገራዊ ለውጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ደ/ር ቢንያም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም፣ ተጨማሪ ስልጠና በመስጠት፣ ከመንግስትና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመስራትም ይሁን በማናቸውም መልኩ ከጎናቸው እንደሆነ በልበ ሙሉነት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡