በአይ.ሲ.ቲ ፖሊሲ ዙሪያ ግምገማ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአይሲቲ (ICT) ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመንና ከወቅቱ ጋር መራመድ የሚችል የሰው ሀይል ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በአይሲቲ መሰረተ ልማትና ተያያዥ በሆኑ መመዘኛዎች ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ተቋማት የጥራት ተሸላሚ በመሆን ምርጥ ከሚባሉ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዘመኑ ጋር እኩል ለመሄድ የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠልና ለሌሎች ተቋማት አርዓያ ለመሆን የሚያስችል በውስጡ በርካታ ዝርዝር ፖሊሲዎች ያሉት “የአይ.ሲ.ቲ ፖሊሲ ግምገማ” ዛሬ ጥቅምት 20/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፣ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ልማት ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሠረት ካሴ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት የመጡ የዘርፉ ሙያተኞች፣ ዲኖችና መምህራን፣ የተለያዮ የአይሲቲ ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
ምቹ ባልሆነ ወቅት (ከኮቪድ ጋር በተያያዘ)ና በአጭር ጊዜ ተቋሙን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የሚችል እራሱን የቻለ የአይሲቲ ፖሊሲ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ተዘጋጅቶ በመቅረቡ ደስተኛ መሆናቸውን ዶ/ር መሠረት በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አሥራት ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡ ዮኒቨርሲቲው ለአይሲቲ መሠረተ ልማት በርካታ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን ዘርፉን ይበልጥ በማዘመን ዩኒቨርሲቲውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ዩኒቨርሲቲነት ለመለወጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር አሥራት አያይዘው አውስተዋል፡፡ ምሑራኑ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው ፖሊሲውን በማርቀቅና በመገምገም በኩል ላበረከቱት አስተዋጽኦ በፕሬዚዳንቱ ዘንድ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
የፖሊሲው ረቂቅ በዶ/ር ተስፋሁን መለሰ ቀርቧል፤ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ምሁራን በረቂቁ ላይ ያላቸውን የግምገማ ሀሳብ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ ባጠቃላይ ጥሩ የሚባል ፖሊሲ እንደሆነ በተሳታፊዎች ዘንድ ተገልጿል፡፡ ቢሻሻሉ ወይም ቢካተቱ መልካም ነው የተባሉ ሀሳቦች በውይይቱ ተጠቁመዋል፡፡በውይይቱ የአይሲቲ ዘርፉን ለማጠናከር ጥሩ የሚባሉ ግብዓቶች መገኘታቸውን ዶ/ር አሥራትና ዶ/ር መሰረት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ረቂቁን በማዘጋጀትም ሆነ በመገምገም ለተሳተፉ ምሁራን እና ተሳታፊዎች ሁሉ ልባዊ ምስጋና በማቅረብ ውይይቱን ቋጭተዋል፡፡
*********************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት 20/2013 ዓ.ም



