በቅድመ-ፅንሰት ጥንቃቄ /Preconception Care/ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት በጎንደር ከተማ አስተዳደር ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅድመ-ፅንሰት ጥንቃቄ / Preconception care/ ዙሪያ ታህሳስ 9 እና 10/2013 ዓ.ም በህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ሲ.ቢ.አር አዳራሽ ስልጠና ሰጠ፡፡
በዚህ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚሰሩ የሚድዋይፈሪ ባለሙያዎች፣የጤና መምሪያና ጤና ጣቢያ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ስልጠናው አቅምን በማጎልበት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል እንደሚያግዝ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስፔ/ሆስፒታል የማህ/አገልግሎት አስተባባሪ ወ/ሪት ቤተልሄም አንተነህ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር ተመሳሳይ ስልጠና ባለፈው አመት መሰጠቱን ያስታወሱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ክሊኒካል ሚድዋይፈሪ ትም/ክፍል ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ መ/ር አየነው እንግዳ፣የአሁኑ ስልጠና ለሁለተኛ ዙር መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ መ/ር አየነው እንግዳ አየይዘውም ከጽንሰት በፊት ጥንቃቄና ህክምና ማድረግ በድህረወሊድ የህጻናት ጤንነት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን እና ያልተፈለገ ውርጃን እንደሚቀንስ እንዲሁም ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በእናቶች ጤንነት ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ያልታወቁና የቆዩ በሽታዎች ካሉ አስቀድሞ ለማወቅና ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ አንዲት እናት ከጽንሰት በፊት ማግኘት ያለባትን አገልግሎት አስመልክቶ የአለም ጤና ድርጅት አስራ ሶስት ፓኬጆች ማስቀመጡን ያነሱት አስተባባሪው፣ የዚህ ስልጠና ዋና አላማም እነዚህን ፓኬጆች ተግባራዊ በማድረግ የተስተካከለ ጽንስ፣ ጤናማ እናት፣ልጅ እና ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስልጠናውን ለመስጠት መታቀዱን አንስተዋል፡፡
ቅድመ እርግዝናን በተመለከተ የተሰጠው ስልጠና የእናቶችንና የጽንስ ሂደትን ጤንነት ለመጠበቅ ለሚሰሩት ስራ ሙያዊ አቅማቸውን እንደሚያጎለብተው የስልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ”በሀገራችን የተለመደው አሰራር ከእርግዘና በኋላ እንክብካቤ ማድረግ ነው”ያሉት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ሚድዋይፍ የሆኑት ዘኪወስ ንጉሴ፣” ከዘር በፊት መሬቱ መዳበርና መዘጋጀት እነደሚገባው ሁሉ አንዲት እናትም ከማርገዟ በፊት ስለራሷ ጤንነት በሚገባ ልታውቅና ልተዘጋጅ እንደሚገባት ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ስልጠናው እጅግ ጠቃሚ ነው”በማለት አብራርተዋል ፡፡
”ምንም እንኳን ስራውን እየሰራውን ብንቆይም ትኩረቱ አነስተኛ በመሆኑ እናቶች በእርግዝናና ከእርግዝና በኋላ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይታያል፣” ያሉት ሌላኛዋ የስልጠናው ተሳታፊ ሲ/ር ገነት ደመላሽ (ከአዘዞ ጤና ጣቢያ)፣ ”የህጻናት መቀንጨር እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የሚከሰቱት በምግብ ማጣት ነው ብየ አላምንም፤ በህ/ሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ ስለሆነ እንጅ ከአርሶ አደሩ ቤት ሁሉ ነገር አለ፣” ይላሉ ፡፡ ስለሆነም እናቶች ቤት ያፈራውን እንዲመገቡ እና አስፈላጊውን ህክምና ቀድመው እንዲከታተሉ የማስገንዘብና የመከታተሉ ተግባር የጤና ባለሙያው እንደሆነ ያብራሩት ሲ/ር ገነት ፣ ይህ ስልጠና ስራውን በእውቀትና በትኩረት ለመስራት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን በጎንደር ከተማ አስተዳደር ደረጃ እየተሰጠ ያለው ስልጠና በቀጣይ ወደሌሎች አካባቢዎችም እየሰፋ እንደሚሄድ የገለጹት የስልጠናው አስተባባሪ መ/ር አየነው፣ ስልጠናውን የወሰዱ ባለሙያዎች በተቻላቸው አቅም ሁሉ ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡
************************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 10/2013 ዓ.ም



