በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ፣ ስትራቴጅ እና እቅዶች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ፣ ስትራቴጅ እና እቅዶች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ከመጋቢት 13-14/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን ያስጀመሩት የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ እንደገለፁት መንግስት የትምህርትን ተደራሽነት ለማስፋፋት ጥረት ቢያደረግም ከፍተኛ የሆነ የጥራትና ብቃት ማነስ እንዲሁም የሚጠኑ የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር መፍታት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ይህን የአፈፃፀም ችግር ሊቀርፉ ይችላሉ ተብለው የታሰቡ ፖሊሲዎችን ፣ስትራቴጅዎችን እና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥቷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ስልጠናውን የወሰዱ የዩኒቨርሲቲ አማራሮች ስልጠናውን ለፈፃሚ አካላት ለማስገንዘብ ከመጋቢት 13-14/2013 ዓ.ም በተለያዩ ርዕሶች ማለትም “የከፍተኛ ትምህርት የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታን” በተመለከተ ፕሮፌሰር ጋሻው አንዳርጌ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ “የሳይንስ ፖሊሲ ስትራተጅና የሳይንስ ልማት ንዑስ ዘርፍ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ” ስልጠና በዶክተር ቢኒያም ጫቅሉ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ “የተቋማዊ አቅም ግንባታ ቁልፍ የተግባር አፈጻጸም አመላካቾች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ቁልፍ ተግባራትን” በተመለከተ አቶ ወንድወሰን በየነ የምህንድስና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ እንዲሁም “በከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ ስትራቴጅና የፕሮግራም ሰነዶች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላና ምደባ ፖሊሲ” በሚል ርዕስ በዶክተር ካሳሁን ተገኘ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካውንስል አባላት በአምስት ተከፍለው በተሰጡት ስልጠናዎች ላይ የተወያዩ ሲሆን በፖሊሲዎች፣ በስትራቴጅዎችና ዕቅዶች ላይ ሊካተቱ የሚገባቸውን፣ የተዘለሉና ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ብለው ያመኑበትን ሃሳብ በውይይቱ ወቅት አቅርበዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎችና ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ሀሳቦች ስልጠናውን የሰጡ አመራሮች መልስ የሰጡ ሲሆን ስልጠናውን በንግግር የዘጉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው በውይይቱ የቀረቡትን ሃሳቦች አድንቀው “ለዕቅዱ መዳበር አስፈላጊ የሆኑት ሃሳቦች ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሚላኩ መሆናቸውንና እንደ ተቋም በተሰጠን እቅድ ላይ ጠንክረን በመስራት ውጤታማ መሆን እንድንችል የሁላችንም ትብብርና ጥናካሬ እንዳይለዬን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡