በሐገር አቀፍ ደረጃ የሆስፒታሎችን አገልግሎት ለማሻሻል እየተሰራ ነው
ከሁለት ዓመታት በፊት “አይኬር” (iCARE) ወይም እኔ ያገባኛል በሚል ስያሜ ሐገራዊ ፕሮጀክት ተቀርጾ በተመረጡ 24 ሆስፒታሎች የመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ ተግባር በመከናወን ላይ ነው።
ይህን በዝግጅት ምዕራፍ ላይ የሚገኘውን የአገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት የፌደራል ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ፣ የሲብል ሰርቪስ፣ የገንዘብ እና ሌሎች ከ7 በላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል አሰራርን መጋቢት 24/2013 ዓ.ም ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
በመቀጠልም በሆስፒታሉ አዲሱን የአገልግሎት ማሻሻያ “I-care” ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋመው ግብረ-ኃይል የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማሻሻል ያመች ዘንድ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የሚስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች በተገኙበት የፖስተር ገልጻ አካሂዷል።
በተጨማሪም በሳይንስ አምባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የውይይትና የጥያቄ መድረክ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በበጀት ዓመቱ በህግ ማስከበሩ ተግባር እና በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ችግሮች ቢደራረቡም ዩኒቨርሲቲያችን በብቃት መወጣት መቻሉን አንስተው በዚህ አስቸጋሪ ሰዓትም ከዪኒቨርሲቲው ጎን ለቆሙ የቁርጥ ቀን አጋሮች እና ባለሙያዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በቀጣይ አገልግሎቱን የበለጠ ለማሻሻልም ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮ፣ ከዘወትር አጋሮች እና ከባለሙያዎቻ ጋር በርብርብ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፉጻሚ ዶ/ር አሻናፊ ታዘበው የቀጣይ የ “i CARE” እቅድን ለተጋባዥ እንግዶች አቅርበው ሰፊ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በተጋባዥ እንግዶች ለተጠየቁ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቶ እና መግባባት ላይ ተደርሶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
