በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነና የተዋደደ ስርአተ ትምህርት ለመቅረፅ የሚያስችል አውደ ጥናት ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቅድመ ምረቃ የህክምናና ጤና ሳይንስ ፕሮግራሞች ሀገር አቀፍ የስርአተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናት ( National Curriculum Evaluation and Harmonization Workshop For Undergraduate Medicine and health science programs) ሚያዚያ18 እና 19/2013ዓ/ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ አካሄደ፡፡

በአውደ ጥናቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ዋና አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው፣ በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት የቅድመ ስራ ስልጠና የዲግሪ ፕሮግራሞች አስተባባሪ ሲስተር አዜብ አድማሱ፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የፕሮግራሞችና የስርአተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አድነው ኤርበሎ፣ከተለያዩ አጋር አካላት፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የሙያ ማህበራትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በርካታ የሆኑ የቅድመ ምረቃና የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ማለትም 33 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 39 የሁለተኛ ዲግሪ፣ 8 የፒ ኤች ዲ ፣ 8 ስፔሻሊቲ፣ 3 ሳብ ስፔሻሊቲ በአጠቃላይ 91 ፕሮግራሞችንና ስምንት ሽ በላይ ተማሪዎችን እያሰተማረ እንደሚገኝ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ያወሱ ሲሆን፣ መንግስት የራሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰበት ባለበት ወቅት ኮሌጁ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲያዘጋጅ ከተሰጡት ሁለት ዋና ዋና ፕሮግራሞች በተጨማሪ በኮሌጁ ፈቃደኝነትና በማህበረሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ በእለቱ ከሚገመገሙት 17 ፕሮግራሞች መካከል ስምንቱ በኮሌጁ የተዘጋጁ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ በአውደ ጥናቱ በርካታ ግብአቶችና ማስተካከያዎች ተሰጥተው ወደተግባር መግባት እንዲቻል ተሳታፊዎች በንቃት እንዲሳተፉ ዶ/ር አሸናፊ አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ ጥራት ያሏቸውን ተመራቂዎች ለማፍራት ዩኒቨርሲቲዎች ጥራቱን የጠበቀ ስርአተ ትምህርት የመቅረፅ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን አያይዘው የሚዘጋጀው ስርአተ ትምህርት ጥራቱ ተጠብቆ የሚመረቁ ተመራቂዎች ጥራት ያላቸውና በማህበረሰቡ ተፈላጊ ሆነው ማህበረሰቡን ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያላቅቁ፣ በተለይም በጤናው መስክ ጥሩ የጤና ባለሙያ ሆነው እንዲወጡ ማስቻል የፕሮግራሙ አንዱ አላማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የፕሮግራሞችና የስርአተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ በአቶ አድነው ኤርበሎ አማካኝነት የጤና ሳይንስ ፕሮግራሞች ስርአተ ትምህርት ቫሊዴሽን አካሄድን አስመልክቶ ገለፃ የቀረበ ሲሆን፣ የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት ለማሻሻል፣ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያሟሉ ተመራቂዎችን ለማፍራት፣የተመራቂዎችን የምርቃት ምጣኔ ለማሳደግ በሚያስችል ደረጃ ለማዘጋጀት፣ በባለድርሻ አካላት ለማስተቸት ገንቢ ግብአቶችን ለማሰባሰብ እንዲሁም ጠንካራ፣ ችግር ፈቺና የተዋደደ ወጥ ስርአተ ትምህርት ለማዘጋጀት አላማ ያደረገ አውደ ጥናት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም 17ቱን የቅድመ ምረቃ የህክምናና ጤና ሳይንስ ፕሮግራሞች በ14 ሴክሽኖች በመመደብ ተሳታፊዎች እንዲገመግሙ፣ ግብአቶችና ማስተካከያዎች እንዲሰጡ ለአንድ ቀን ተኩል ያህል እንዲገመግሙ ከተደረገ በኋላ በአጠቃላይ መድረኩ በቡድን ተወካዮች አማካኝነት ቀርቦ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡
