“ራሳችንና ሌሎችን ከጫትና ከአደንዛዥ እፆች እየጠበቅን ብሩህ ተስፋ ያለው ትውልድ እንፍጠር” በሚል ርዕስ በወረታ ከተማ ስልጠና ተሰጠ
“ራሳችንና ሌሎችን ከጫትና ከአደንዛዥ እፆች እየጠበቅን ብሩህ ተስፋ ያለው ትውልድ እንፍጠር” በሚል ርዕስ በወረታ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ ግለሰቦች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት አዘጋጅነት ህዳር 17 እና 18/ 2013 ዓ.ም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
የስልጠናው አስተባባሪ እና በፋርማሲ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ እሸቴ መለሰ እንደገለፁት አደንዛዥ እፆችን መጠቀም ማህበራዊ ጉዳትን የሚያስከትል በመሆኑ የዛሬው ስልጠና ለወረታ አካባቢ ነዋሪዎች የጫት መቃም ምን ያህል በህብረተሰቡ ውስጥ እንደተስፋፋና ጎጅነቱን በማሳዬት ህብረተሰቡ ለጉዳዩ ትኩረት ሠጥቶ እና እርስ በእርስ ተደጋግፎ ይህን አስከፊ ሱስ ለማሰወገድ ሞዴል ወጣቶችን በመፍጠር አርያነት ያለው የመከላከል ስራ ለመስራት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሰነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ንጉሴ ይግዛው በበኩላቸው ጫት መቃም በጤና፣ በማህበራዊ ኑሮ እና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ከመሆኑ በላይ የሰውን ልጅ ኑሮ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የጉዳዩን ጥልቀት እንዲረዱ በማድረግና ችግሩን በማወቅ መፍትሄ ለማግኘት ከፍተኛ እገዛ ያለው መሆኑ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለተወጣጡ ሰዎች ስልጠናውን የሰጠን ሲሆን ህብረተሰቡም በቁርጠኝነት ይህን ጎጅ ተግባር በመታገል ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን እኛ እንደመነሻ የችግሩን አሳሳቢነት ካሳዬን ራሱ ህብረተሰቡ በተደራጀ መልኩ የመከላከል ስራውን ያከናውናል ብለንም እናምናለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የስብሰባው ተካፋይ የሆኑት መምህር ወርቁ ማንደፍሮ እንደገለፁት በወረታ አካባቢ ያለው የጫት መቃም ተግባር በሁለት መልኩ ይገለፃል፡፡ አንደኛው በጭንቀት ሌላኛው በቅብጠት ይፈፀማሉ፡፡ በጭንቀት የሚሆነው ተምሮ ስራ በማጣት፣ ቤተሰባዊ ችግር አጋጥሞት፣ ጎዳና በመውጣትና ተያያዥ ችግሮች ሲሆን በቅብጠት የሚቃመው ደግሞ ለመዝናናት፣የከተማ ልጅ ስልጡን ለመባል ጓደኛን ለማስደሰት በሚሉ ምክንያቶች እየተፈፀሙ ያሉ በመሆናቸው እነዚህ ተግባራት እኛንና ልጆቻችንና አጠቃላይ ህብረተሰቡን የሚጎዱ በመሆናቸው ልንከላከላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የስልጠናው ተካፋይ የሆኑት አቶ ጌትነት ሞላ የተባሉት የወረታ 2ኛ ደረጃ መምህር እንደተናገሩት ለችግሩ ዋና ምክንያት ስራ አጥነት መሆኑን ከገለፁ በኋላ ይህን በማየትና የችግሩን ስፋት በመመልከት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህን ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠቱ ተደስቻለሁ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከሌሎች ሠልጣኞች መረዳት እንደተቻለው ከአሁን በፊት በወረታ አካባቢ ብዙ የጫት ምርት ያልነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በደራ ፎገራ አለም በር ዙሪያ ሁሉ እየተመረተ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ አየሆነ መጥቷል ብለዋል ፡፡ በአካባቢያችንም በቂ የመዝናኛ ቦታዎች ባለመኖሩ ወጣቱ ለጫትና ተያያዥ ጉዳዮች ተጋላጭ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው የልጆች አስተዳደግ ላይም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከቤቱ ጀምሮ ቁጥጥር በማድረግና አካባቢያችን ከጫትና ከአደንዛዥ እፅች መጠበቅ ይገባናል ሲሉ አስረድተዋል ፡፡
* * * * * * * * * * * * * * * * * * * *
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም

