ለ2008 ዓ.ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ2008 ዓ.ም አዲስ ተማሪዎች በ2ኛዉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና ተዛማጅ ርዕሶች ዙሪያ ከጥቅምት 03-05/2008 ዓ.ም ስልጠና ሰጠ፡፡ በስልጠናዉ ከ2ኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተጨማሪ የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ስራዎችና ባለድርሻዎች ሚና፣ የዩኒቨርሲቲዉ የ2008 ዓ.ም ዕቅድ፣ የተቋማዊ ለዉጥ ትግበራ እስከ አሁኑ አፈፃፀም፣ የአመራሩ ሚና እና ቀጣይ አቅጣጫዎች፣ የለዉጥ አስተሳሰብ ግንባታ በሚሉ ርዕሶች ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በየመሃሉ በየርዕሶች የዉይይት መድረክ በመክፈት ሰፊ ዉይይትና ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡
በስልጠናዉ የተሳተፉት የዘንድሮ አዲስ ተማሪዎች 6000 (ስድስት ሺ) ሲሆኑ ስልጠናዉ በማኪራ ግቢ፣ በአፄ ቴዎድሮስ ግቢ፣ በአፄ ፋሲል ግቢና በመለስ ዜናዊ ግቢ ተሰጥቷል፡፡
የስልጠናዉን አፈፃፀምና ፋይዳ አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲዉ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ሲገልፁ ከዚህ በፊት ይህን መሰሉ ስልጠና ለመምህራን፣ ለአስተዳደር ሰራተኞችና ለነባር ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን አሁንም ለአዲስ ተማሪዎች ስልጠናዉን በተሳካ ሁኔታ ሰጥተናል፤ ካሉ በኋላ የአሁኑ ለአዲስ ተማሪዎች የተሰጠዉ ስልጠናም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸዉ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የአቅም ስንቅ አንዲሆናቸዉና በተለይም በ2ኛዉ ዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት ዉስጥ ተመርቀዉ ወደ ስራዉ ዓለም የሚቀላቀሉ እንደመሆናቸዉ ሀገራዊ ራዕይና ዕቅድ ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸዉ ለአገራችን የዕድገት ጉዞ በራሳቸዉ ሊኖር የሚገባዉን ተሳትፎ የሚያጠናክር እንዲሆን ያለመ ነዉ ብለዋል፡፡
በስልጠናዉ ተሳታፊ ከነበሩ አዲስ ተማሪዎች ጥቂቶችን አነጋግረናል፡፡ ሁሉም የሀገራችንን 2ኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዕዉቀት መጨበጣቸዉ ለራሳቸዉ፣ ለተቋማቸዉና ለሀገራቸዉ የበኩላቸዉን በዕዉቀት ላይ ተመስርተዉ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸዉ እንደሆነ በአጠቃላይ በስልጠናዉ መደሰታቸዉን ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶት