ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛና መሰረታዊ አመራሮች ከመጋቢት 24 እስከ 27 /2010 ዓ.ም የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት፣ በመልካም አስተዳደር ትግበራ፣ በዜጎች ቻርተር ዝግጅት ፅንሰ ሀሳብና አተገባበር እንዲሁም በሌሎች ተያያዠ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡ በስልጠናውም 144 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
የኢፌድሪ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 24 እስከ የካቲት 1/ 2010 ዓ.ም ባዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊ የነበሩት አቶ ፈንታሁን ጫኔ የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ጋሻው ነበሩ የፕላንና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንዲሁም አቶ አልማው አላበ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስልጠናውን በቅንጅት ሰጥተዋል፡፡
[widgetkit id=8840]
ስልጠናው በዩኒቨርሲቲያችን ከተቋማዊ የለውጥ እንቅስቃሴና ከመልካም አስተዳደር ትግበራ አንፃር እየተከናወኑ የሚገኙ በርካታ ስራዎችን ለማጠናከር፣ የአቅም ግንባታና የማስፈፀም አቅምን በመፍጠር በተለይ አመራሩና በየደረጃው የሚገኙ ፈፃሚ አካላት የበለጠ የለውጡን ስራና የመልካም አስተዳደሩን ተግባር በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ለማድረግ የታሰበ ስልጠና መሆኑን አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ፣ መካከለኛና መሰረታዊ አመራሮች የተቋማዊ ለውጡንና የመልካም አስተዳደሩን ስራ የበለጠ በባለቤትነት ይዘው እንዲቀሳቀሱና በተለይም በስራቸው የሚገኙ ፈፃሚ ሰራተኞችን በማብቃት በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲያችን የተቋማዊ ለውጥ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ግንባታ የበለጠ እንዲሻሻልና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ከሰልጣኞች እንደሚጠበቅ አቶ ፈንታሁን ጫኔ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ወደፊት ለፈፃሚ አካላት ለሚሰጠው የስልጠና መርሀ ግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ካሁን በፊት ተጀምረው የነበሩ ስራዎችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ለቀጣይ አፈፃፀምም ጥሩ መሰረትእንደሚሆን በስልጠናውን ሲሳተፉ ያገኘናቸው አቶ ዳዊት ዳርጌ ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት