ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳት፣ ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያውያን ሴንተር ዊዝ ዲስኤብሊትስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት (Ethiopians center with disabilities & development) ጋር በመተባበር፣ ለ2010 ዓ.ም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከጥቅምት 3 – 5/2010 ዓ.ም አዘጋጅቷል፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ አካል ጉዳት፣ ጥናት እና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ህይወት አበበ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ እርሳቸው የሚመሩት ቢሮ ለዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በራሳቸው እንዲተማመኑ እና በማንኛውም መስክ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ እና የተለያዩ የጽህፈት መሳሪያዎች እንዲያገኙ ማድረግ፤ የላውንደሪ እና የነጻ ኮፒ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ለአብነት ከሚጠቀሱ ድጋፎች መካከል መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ህይወት ለተማሪዎቹ መልካም የትምህርት ጊዜ የተመኙ ሲሆን አያይዘውም በቆይታቸው ብቁና ተወዳዳሪ በመሆን ውጤታማ ሁነው ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ አሳስበዋል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል ያንተአምላክ መላኩ እና ዋሴ እውቀት የተባሉ የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተደረገላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅት እና በቀረበላቸው ትምህርት አዘል በሆኑ ስነ ጥበባዊ ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተሰጣቸው ስልጠናም በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
በአምሳሉ ግዛቸው