ለአለፋና ጣቁሳ ግብርና ሙያተኞች ስልጠና ተሰጠ
የግብርናው ኢኮኖሚ እንደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ሁሉ ለሀገር እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ይህ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው ግብርና ከሰማኒያ በመቶ በላይ ለሆነው የሀገራችን የህብረተሰብ ክፍል ዋነኛ የገቢ ምንጭ ቢሆንም በዘመናዊ ሳይንስና መሳሪያ በመታገዘ በኩል ውስንነቶች እንዳሉበት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ወደ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን – አለፋና ጣቁሳ ወረዳዎች በመሄድ ለአርሶ አደሮችና ለግብርና ሙያተኞች የመስኖ ሀብት ልማትን የተመለከተ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
ስልጠናው ከህዳር 24 እስከ ህዳር 25/2013 ዓ.ም በሻውራ ከተማ የተሰጠ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሰቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፋንታው፣ የአለፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በጋሻው ይመር፣ የዩኒቨርሲቲው ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን፣ የአለፋና የጣቁሳ ወረዳዎች ግብርና ሙያተኞችና ባለድርሻ አካላት በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በአቶ በጋሻው ተደርጓል፡፡ የአለፋና የጣቁሳ ወረዳዎች እምቅ የሆነ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ናቸው፤ ስለሆነም የአካባቢው ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ በዩኒቨርሲቲው በኩል ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲደርግላውቸው አቶ በጋሻው በንግግራቸው አሳስበዋል፡፡
አቶ ሰሎምን ፋንታው ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የጣና ኃይቅ በወረዳዎቹ (አለፋና ጣቁሳ ወረዳዎች) ዳርቻ እንደመገኘቱ መጠን ህብረተሰቡ ከሀይቁ በበቂ ሁኔታ እየተጠቀመ አይደለም፤ በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ስለ መስኖ ሀብት ልማት አጠቃቀምና ተያያዝ ዘርፎች ለአርሶ አደሮችና ለግብርና ሙያተኞች ስልጠና እንዲሰጥ አድርጓል ብለዋል፡፡ አቶ ሰሎሞን አያይዘውም አጥጋቢ የሆነ የመስኖና የውሀ አጠቃቀም እውቀት ሲኖር፣ ህብረተሰቡ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት ስራ ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋል፣ የነቃ የስራ ባህል ካለ ደግሞ የማህበረሰቡ የኑሮ ሁኔታ በቀላሉ እንዲሻሻል ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከአነጋገርናቸው ሰልጣኞች መካከል የጣቁሳ ወረዳ የአትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አቶ አወቀ መከተና የአለፋ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ አማረ ላቀው የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቦታው ድረስ በመምጣት የመስኖ ሀብት ልማትንና ተያያዥ ሙያዎችን በተመለከተ በንፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ሙያዊ የስራ ላይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ስለሰጡን ልባዊ ምስጋና ይደረሳቸው ብለዋል፡፡
****************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 26/2013 ዓ.ም



