ለሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ሙያተኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞችን የሙያ ብቃትና የስራ ተነሳሽነት ይበልጥ በመጨመርና በማጎልበት ብሎም በአዲሱ የበጀት አመት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የማነቃቂያና የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ለተለያዩ የስራ ክፍሎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲው የነጥብ ስራና ደረጃ አወሳሰን (ጄ.ኢ.ጅ) ትግበራና አፈጻጸም ግምገማን በተመለከተ ውይይት ለማካሄድና የሰው ሀብት አሰራሩንም ሆነ መረጃ አያያዙን ይበልጥ ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ዛሬ ነሀሴ 29/2012 ዓ.ም በሁሉም ግቢዎች ለሚገኙ የሰው ሀብት ስራ አስተዳደርና ልማት ሙያተኞች መሰጠት ጀምሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ የውይይቱንና የስልጠናውን አስፈላጊነት በመግለጽ የዕለቱን መርሀ-ግብር በንግግር አስጀምረዋል፡፡

በጠዋቱ መርሀ-ግብር የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አስማማው በቅርቡ በተቋሙ ተግባራዊ ስለ ሆነው የነጥብ ስራና ድልድል አጠር ያለ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ለወደፊት ይበጃሉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦች በውይይቱ ተነስተዋል፤ የአሰራር አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

የክፍሉን አጠቃላይ አሰራርና የመረጃ አያያዝ ይበልጥ ለማዘመን የሚያስችል የአይሲሚስ (ICSMIS – Integrated Civil Serves management Information System) የተሰኘ ሶፍት ዌር አተገባበር ስልጠና፣ ከፌደራል ሲቪል ሰርቪስ በመጡ ሙያተኞች ከሰዓት በኋላ ጀምሮ መሰጠት ጀምሯል፡፡ ይኸው መርሀ ግብር እስከ ጳጉሜ 1 ቆይታ ይኖረዋል፡፡