የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የካሮሊንስካ የእናቶችና የህጻናት የጤና አገልግሎት ተቋም በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲና ስዊድን ሀገር የሚገኘው የካሮሊንስካ ተቋም በጋራ ለመስራት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት መስከረም 30/2010ዓ.ም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በጋራ ለመስራት የተፈራረሙበት የሙያ መስክ በሚድዋይፈሪ ሙያ የፒኤችዲ ፕሮግራም መክፈትና ስልጠና መስጠት መሆኑን የሁለቱም ተቋም ተወካዮች በውይይታቸው ላይ አንስተዋል፡፡

የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤናን ሽፋን ከፍ ለማድረግና በተለይም የእናቶችንና የህጻናትን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መሆኑን የስምምነት ሰነዱ ያትታል፡፡ በተጨማሪም የፒኤችዲ ፕሮግራሙ መከፈት የእናቶችንና የህጻናትን የጤና ችግር በጥናትና ምርምር እገዛ ለመፍታት እንዲሁም ሀገሪቱ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ ያወጣችውን የረዥም ጊዜ ዕቅድና ፖሊሲ ለማስተግበር እንደሆነ ይታመናል፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካና የአካዳሚ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፣የህክምናና ጤናሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩና ከስዊድን ሀገር የካሮሊንስካ ተቋም ተወካዮች ናቸ፡፡

ፕሮግራሙ በፒኤችዲ የሚድዋይፈሪ ሙያ በሚደረገው የጥናትና ምርምር ስራ ከፍተኛ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖርና ለሀገሪቱ ፖሊሲ ግብና ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በጨማሪም ባለው ማቴሪያል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠትና በህክምና ሙያው ቁጥጥር እንዲኖር ለማድረግም ጠቀሜታ አለው፡፡

በስምምነቱ መሰረት በዚህ ፕሮግራም ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ በጀት መፍቀድ፣ ብቃት ያላቸውን አማካሪ ማደራጀትና የትምህርት ክፍሉን ሰልጣኞች መመልመልና ማዘጋጀት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት ሲሆን በካሮሊንስካ ተቋም በኩል ደግሞ ዕውቀትና ልምዱን ለማሸጋገር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚድዋይፈሪ ሙያ በፒኤችዲ ፕሮግራም ለሚሰለጥኑት ተማሪዎች የተሻለ ዕውቀት ሊያሰተለላልፉ የሚችሉ ምሁራንን የማዘጋጀት፣ ዲፓርትመንቱ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ሥርዓተ ትምህርት የመቀረፅና የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የጥናትና ምርምር አማካሪ የመሆን ኃላፊነት አለው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የካሮሊንስካ ተቋም ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት በጋራ እንደሚሰሩ በስምምነቱ ላይ ተገጿል፡፡

በስዊድን ሶልና ግዛት የተመሰረተው የእናቶችና የህጻናት የጤና አገልግሎት ትምህርት ክፍል በዓለም ከሚገኙት የህክምና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ከዚህ ተቋም ጋር መስራትውጤታማ ተግባርን ለማከናወን እንደሚረዳ በስምምነቱ ማጠቃለያ ላይ ተገጿል ፡፡

ዘጋቢ፡-ሳሙኤል ማለደ

ትረጉም፡- በላይ መስፍን

ኤዲተር፡- ደምሴ ደስታ

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት